የሬዲዮ ዘመቻ እንዴት መፍጠር እንደሚቻል

ዘመቻ ምንድን ነው?

ዘመቻ ማለት ተቋማት ወይም ግለሰቦች የተወሰኑ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ለማሳመን ወይም በአንድ የተወሰነ ርዕስ ላይ ያላቸውን አመለካከት ለመቀየር የተደራጀ፣ በጊዜ-የተገደበ ጥረት ነው። ዘመቻዎች የተመረጡ ዓላማዎች ሲኖሯቸው አብዛኛውን ጊዜ በአንድ ትልቅ ለውጥ ወይም ድርጊት ላይ ያተኮሩ ናቸው። ዘመቻዎች በሬዲዮ አጭር ማስታወቂያ፣ በቃለ መጠይቅ፣ የቤት ለቤት ወይም በማህበረሰብ ዘንድ ጉዳዮች ላይ በመወያየት፣ ተከታታይ ማስታወቂያዎች በጋዜጦች ወይም በብሮሹሮች እና በሌሎችም መልኩ ሊከወኑ ይችላሉ። ተመራጭ ዘመቻዎች ጥቂት የተለያዩ ሚዲያዎችን በማጣመር ለብዙ ሰዎች ተደራሽ መሆን ይችላሉ።

ተመርችጭ ዘመቻዎች በተቻለ መጠን በርካታ ሰዎችን ለመድረስ የተለያዩ ሚዲያዎችን ያጣምራል።

ዘመቻ መቼ ጥቅም ላይ መዋል አለበት?
አንድ የሬዲዮ ጣቢያ ወይም ሌሎች አካላት በማህበረሰባቸው ላይ አዎንታዊ ለውጥ ያመጣል ብለው የሚያስቡት የተለየ ተግባር ወይም አመለካከት ሲኖራቸው ዘመቻን መጠቀም ይገባል። ዘመቻዎች ለማቀድ እና ለማስፈጸም ጊዜ፣ ጉልበት እና ጥረት ይጠይቃሉ። ውጤታማ እንዲሆኑ ከተፈለገ ከመደበኛ ፕሮግራም ውጪ ተጨማሪ ጥረት ያደርጋሉ። በለውጥ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር በምትጥሩባቸው አካባቢዎች ከሚሰሩ የሀገር ውስጥ ድርጅቶች ጋር መተባበር እርስዎን እና አድማጮችዎን ይጠቅማል።

ለምሳሌ ከመጋቢት 2014 ጀምሮ ማላዊ ከአንድ አመት በላይ በተደረገ ዘመቻ ንቁ ብሄራዊ የክትባት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ከ10 በመቶ ያነሰ ህዝቧ ተከትቦ ነበር። ይህ ቁጥር ማላዊ ከሰበችው 70 በመቶ ህዝቧን የመከተብ ዕቅድ በእጅጉ ያነሰ ነበር። በመሆኑም ክትባቱ የሚሰጣቸው ሰዎች ቁጥርን ለመጨመር ዘመቻ ያስፈልጋል። የዘመቻው አላማ ሰፊውን ህዝብ - ወንዶች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣እንዲሁም አረጋውያን እንዲከተቡ ማበረታታት ይሆናል።

የሬዲዮ ዘመቻ አድማጮቼን በተሻለ መንገድ እንዳገለግል እንዴት ሊረዳኝ ይችላል?

  • የሬዲዮ ዘመቻ አድማጮች እንዲያስታውሱት እና እርምጃ እንዲወስዱ ብዙ ጊዜ የሚደጋገሙ ቁልፍ መረጃዎችን ያሰራጫል።
  • በዘመቻ በኩል ስለ ምርቶች ወይም አገልግሎቶች ግንዛቤን ማሳደግ፣ የአመለካከት ለውጥን ማምጣት እንዲሁም ትግበራን ለማሳካት ጥሪ ማቅረብ ይችላል።
  • ዘመቻ የማህበረሰብ ውይይትን ሊያበረታታ ወይም በህብረተሰቡ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ውይይት ሊያንፀባርቅ ይችላል።
  • የዘመቻ መልእክቶች በተለያዩ ቅርፀቶች ሲዘጋጁ እና በተለያዩ የሬድዮ ፕሮግራሞች በፕሮግራም አነዳደፍ መርሃ ግብር ውስጥ ሲካተቱ ሬድዮ የማዳመጥ ባህላቸው ሊለያይ ለሚችለው የታለመላቸው ታዳሚ ብዙዎችን የመድረስ እድላቸው ሰፊ ነው።

የሬዲዮ ዘመቻ የተሻለ የሬዲዮ ፕሮግራሞችን እንዳዘጋጅ እንዴት ይረዱኛል?

  • ዘመቻዎች ስለታሰቡት አድማጮች የተሻለ ግንዛቤ እንዲያገኙ ያግዝዎታል።
  • ዘመቻዎች ስለ ባለድርሻ አካላት እና ፍላጎቶቻቸው የተሻለ ግንዛቤ እንዲያገኙ ያግዝዎታል።
  • ዘመቻዎች ምን አይነት ቅርጸቶችን እንደሚጠቀሙ እንዲሁም የትኞቹን ባለሙያዎች እንደሚያሳትፉ የመለየቱን እድል ይፈጥራሉ።
  • ዘመቻዎች በሬዲዮ ጣቢያው ውስጥ ትብብርን እና የቡድን ስራን የሚጠይቁ እንዲሁም ለብዙ ፕሮግራሞች ይዘትን ለማዳበር ግብዓቶችን ለማሰባሰብ ያስችላሉ።
  • የሪዲዮ ዘመቻዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚዘጋጁት በተለያዩ አጋሮች ድጋፍ ሲሆን ይህም ለጣቢያው በአጠቃላይ የሚጠቅም እና አዘጋጆች በአጠቃላይ መደበኛ ፕሮግራሞቻቸውን የሚያዘጋጁበትን መንገድ ያጠናክራል።
  • የሪዲዮ ዘመቻዎች አድማጮችን ወደ ሌሎች ፕሮግራሞች መሳብ ይችላል። የፕሮግራም አቅራቢዎች በዘመቻ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት እና ቀጣይ ክፍሎቻቸውን ለማስተዋወቅ ከጣቢያቸው በሌሎች ፕሮግራሞች ላይ እንግዶች ሆነው ይቀርባሉ።

እንዴት መጀመር እችላለሁ?

  1. የዘመቻውን አላማ(ዎች) ያቀናብሩ፦ ዘመቻ ዓላማው አንድን የተወሰነ ዓላማ ለማሳካት ነው። ተቋሞች ወይም ግለሰቦች ወደ አላማውን በሚመለከት እርምጃ እንዲወስዱ ተጽእኖ ለማድረግ ያለመ ነው። የተሳካ የዘመቻ አላማ ምን መለወጥ እንዳለበት፣ ዘመቻው ለተፈለገው ለውጥ እንዴት አስተዋፅዖ እንደሚያደርግ እና የዘመቻውን ባለድርሻ አካላት በግልፅ ይገልጻል።
  2. ታዳሚዎችዎን ይወቁ፦ ዘመቻዎ ውጤታማ እንዲሆን የታለመላቸውን ታዳሚዎች መግለፅ እና መረዳት እንዲሁም እነሱን ለመድረስ የሚቻለውን የመገናኛ መንገዶችን፣ መሳሪያዎች እና ቴክኒኮችን መምረጥ ይኖርቦታል። አድማጮችዎን ሲረዱ፣ መልእክቶቹን፣ ሂደቶቻቸውን እና መሳሪያዎቻቸውን በልበ ሙሉነት ለተለያዩ ዒላማ ታዳሚዎች ማስማማት ከመቻላቸውም በላይ ሁሉንም የታለመላቸው ታዳሚ ክፍሎች ለማነጋገር የተለያዩ ቴክኒኮችን መጠቀም ይችላሉ።
  3. መፈክር ይፍጠሩ፦ አንድን ሃሳብ ወይም አላማ የሚገልጽ የማይረሳ መፈክር ወይም አባባል። መፈክርን የመጠቀም አላማ የታለሙትን ታዳሚዎች እርምጃ እንዲወስዱ ማሳመን ነው።
  4. ስትራቴጂ ይንደፉ፦ ይህ በርካታ ውሳኔዎችን ማድረግን ያካትታል - ለምሳሌ መጠቀም የሚፈልጓቸውን ቅርጸቶች፣ እያንዳንዱ ፎርማት ምን ያህል ጊዜ ጥቅም ላይ እንደሚውል፣ ምን አይነት ፕሮግራሞች እንደሚካተቱ፣ ምን ሌሎች የመገናኛ መሳሪያዎች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ፣ ወዘተ. . .
  5. የዚህ አይነት ዘመቻ ላይ ሊደረጉ እና ላይደረጉ የሚገቡ፦

ዝርዝሮች

1. የዘመቻውን ዓላማ (ዎች) ያዘጋጁ

እያንዳንዱ ዘመቻ ዓላማ ኖሮት ነው የሚነሳው፦ እያረጉት ያለው ጥሪ ምንድነው? አድማጮችዎ ምን እንዲያደርጉ ወይም እንዲያውቁ እየጠየቋቸው ነው ወይም ምን ዓይነት አመለካከት እንዲይዙ ተጽዕኖ ለማድረግ እየሞከሩ ነው? ይህ ዘመቻ የተወሰኑ አድማጮች ላይ ያነጣጠረ ነው? እነዚህን ነገሮች ማወቁ ከተለያዩ አድማጮችዎ ጋር የሚስማሙ መልዕክቶችን እንዲያዘጋጁ ይረዳዎታል።

በዘመቻዎ ምን ማከናወን እንደሚፈልጉ ግልጽ ለማድረግ እራስዎን ጥያቄዎችን ይጠይቁ።

ዘመቻ ከመጀመርዎ ወይም ከመቀላቀልዎ በፊት የሴቶች ልማት ማህበር - 1995 የሚመክሯቸው አንዳንድ ጥያቄዎች ቀጥለው ይገኛሉ። ፋርም ሬዲዮ ኢንተርናሽናል ለዚህ ሰነድ ዓላማ ሲባል ጥያቄዎቹን እንደሚከተለው አስተካክሎ አስፋፍቷቸዋል፦

  • ይህን ዘመቻ ለምንድነው የምቀላቀለው/የምፈጥረው?
  • የምጠብቃቸው ውጤቶች ምንድን ናቸው? ስኬቱ ምን ይመስላል?
  • ይህ ዘመቻ ማንን/ምንን እየደገፈ ነው?
  • ዘመቻውን የሚደግፈው ማነው እና ለምንስ ነው?
  • ሰዎች እርምጃ እንዲወስዱ ወይም እንዲወስኑ ምን የተለየ እርምጃዎችን እየሞከርን ነው?
  • ይህ ዘመቻ በተለያዩ ደረጃዎች የተደገፈ እና በየእለቱ በሚደረጉ ትግሎች ላይ የተመሰረተ ነው ይህም የዘመቻውን ግብ በተሳካ ሁኔታ በማሳካት ሊሻሻል ይችል ይሆን?
  • ይህ ዘመቻ ስልታዊ ወቅትን ወይም የተለየ የፖለቲካ ቦታን ለጉዳዩ አመቺ በሆነ ሁኔታ ጥቅም ላይ ያዋለ ነው?
  • ዘመቻው ግንዛቤን ያሳድጋል? ዜጎች ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ላይ ያላቸውን ተሳትፎስ ያበረታታል?
  • ዘመቻው በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለውን የስልጣን ግንኙነት ለመቀየር አስተዋፅዖ ይኖረዋል? በሀብታም እና ድሃ? እረኞች እና ገበሬዎች? ወዘተ...
  • በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ በሌሎች እየተካሄደ ያለ ዘመቻን የመድግም ወይም የመፎካከር እድሉ ሊኖር ይችላል?
  • የዕርስዎ ድርጅት ወይም ህብረትዎ በጉዳዩ ላይ ዘመቻ ካላደረገ ሌላ ዘመቻውን ሊያንቀሳቅስ የሚችል ይኖራል?
  • ጥሩ የስኬት ታሪክ ያለውን ዘመቻ በመቀላቀል ጊዜ እና ሃብት በተሻለ ሁኔታ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል?
  • ጉዳዩን ለመፍታት ይህ ትክክለኛው ጊዜ ነው? በዚህ ጊዜ በጉዳዩ ላይ ዘመቻ ካላደረጉ ምን ሊሆን ይችላል?
  • እርስዎ ወይም ህብረትዎ በጉዳዩ ላይ ዘመቻ ለማድረግ አስፈላጊውን እውቀትና ክህሎቶችን ጨምሮ አስፈላጊውን ግብአት ማሰባሰብ ይችላሉ?
  • የዘመቻ አዘጋጅ ቡድኑ ስለ ስኬታማነቱ ምን ያህል ይተማመንበታል? (የስኬታማነት እድሉ ጠባብ ነው ብለው ካሰቡ ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ወይም አካሄዶችን ግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው።)

የዘመቻውን ዓላማዎች ለመወሰን እንዳዎት ሌሎች ሊጠይቋቸው የሚችሉት ጥያቄዎች ምንድን ናቸው?

አድማጮችዎን ይወቁ

አድማጭዎችዎን ማወቅ ለዘመቻዎ ስኬት ቁልፍ ነው። ስለ ታዳሚዎ እና ከዘመቻው ርዕስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ባወቁ መጠን ወደ እነርሱ የሚደርስ ዘመቻ ለመንደፍ እና አመለካከታቸውን እንዲቀይሩ ወይም እርምጃ እንዲወስዱ ለማሳመን የበለጠ እድል ይኖርዎታል።

የትኞቹን የሬዲዮ ፕሮግራሞች ማን እንደሚያዳምጥ እና አድማጮችዎ ከዘመቻው ርዕስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ጨምሮ ስለ አድማጭዎችዎ የቻሉትን ያህል መረጃ ይሰብስቡ። ዘመቻዎ የሚያተኩረው በአንድ የተወሰነ አድማጭ ላይ ከሆነ፣ ለምሳሌ አዋቂ ሴቶች ላይ፣ በነሱ አድማጮች እና በሚያዳምጧቸው ፕሮግራሞች ላይ ብቻ ያተኩሩ። ለመላው ጣቢያ የሚሆን ለሁሉም ሰው ለመድረስ ለታቀደ ዘመቻ በሁሉም የአድማጭ ቡድኖች ላይ ጥናት ያድርጉ።

ለዘመቻዎ የታዳሚን መገለጫ ለመፍጠር ሊጠቀሙባቸው የሚችሏቸው ጥያቄዎች እንደሚከተሉት ናቸው።

  • የእርስዎ የስፖርት ፕሮግራም የተለመዱት አድማጮች እነ ማን ናቸው? የወጣቶች ፕሮግራም? የሙዚቃ ፕሮግራም? የፖለቲካ ፕሮግራም? የገበሬ ፕሮግራም? የጤና ፕሮግራም?
  • ወንዶች ብዙውን ጊዜ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማቸዋል? ወንዶች እርምጃ እንዲወስዱ ወይም አመለካከታቸውን እንዲቀይሩ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው? ወንዶች ምን ጥርጣሬዎች ወይም ፍርሃቶች አሏቸው?
  • ስለ ሴቶችስ? አመለካከታቸው ወይም ልምዳቸው ከወንዶች የተለየ ነው? የተለያዩ ነገሮች ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ያነሳሳቸዋል ወይንስ አመለካከታቸውን ይለውጣሉ? የተለዩ መሰናክሎች ያጋጥሟቸዋል? ምን ጥርጣሬዎች ወይም ፍርሃቶች አሏቸው?
  • ስለ ወጣቶችስ? በዚህ ርዕስ ላይ ምን ይሰማቸዋል? የተለያዩ ነገሮች እርምጃ እንዲወስዱ ያነሳሳቸዋል? የተለዩ መሰናክሎች ያጋጥሟቸዋል? ምን ጥርጣሬዎች ወይም ፍርሃቶች አሏቸው? ወጣት ወንዶች እና ወጣት ሴቶች የተለያዩ አመለካከቶች፣ ጥርጣሬዎች እና ፍርሃቶች አሏቸው? እርምጃ ለመውሰድስ የተለያዩ ነገሮች ናቸው የሚያነሷሷቸው?
  • በአንድ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ከዚህ ርዕስ ወይም አመለካከት ጋር የተለየ ግንኙነት አላቸው? አንድ ሀይማኖት ወይም እንደየብሄራቸውስ ርዕሱ ላይ ያላቸው አመለካከት ይለያል?
  • በተወሰኑ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ሰዎች በዚህ ርዕስ ላይ የተለየ አመለካከት አላቸው? እርምጃ የመውሰድ ዕድላቸው ሰፊ ወይስ ጠባብ ነው?

ለበለጠ መረጃ የስርጭት ባለሙያ መመሪያውን ያንብቡ

ይህ መረጃ የትኛዎቹ ፕሮግራሞች እና መልዕክቶች የተመረጡ አድማጮችን ለመድረስ እና እርምጃ እንዲወስዱ ለማነሳሳት የሚጠቀሙበት እቅድ ለመፍጠር ያግዝዎታል። ይህንን መረጃ በሠንጠረዥ ውስጥ ማደራጀት ይችላሉ።

3. መፈክር ይፍጠሩ

መፈክር አጭር እና የማይረሳ ሀረግ ነው፣ ብዙ ጊዜ በማስታወቂያ ላይ ጥቅም ላይ ይውላል፣ ለዘመቻዎችም አስፈላጊ ነው። በማስታወቂያ ላይ፣ የናይክ "አድርጉት" መፈክር በሁሉም ማስታወቂያዎቻቸው ላይ ይታያል፣ የማክዶናልድ "እየወደድኩት ነው" እሚለውም መፈክር እንደዛው በየማስተዋወቂያቸው ይታያል። ባራክ ኦባማ "አዎ እንችላለን!" የሚለውን መፈክር እንደ 2000 የፕሬዝደንት ዘመቻ መፈክር ተጠቅመዋል። ምንም እንኳን መፈክሩ እንደየፕሮግራሞቹ አይነት ቢለያይም መፈክሩ እርስዎ ለመድረስ እየሞከሩ ያሉትን ዋና አድማጮች በተከናወኑ ጥናቶች መሰረት ሊስብ ይገባል። መፈክሩ አድማጮች ሲሰሙት የዘመቻዎትን ዋና መልእክት እንዲረዱ የተግባር ጥሪዎን ማካተት አለበት።

የዘመቻው መፈክር ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ የዘመቻዎ ዋና መልእክት ትክክለኛ መሆን አለበት።

ዋናው መልእክት ሶስት ነገሮችን ማካተት አለበት፦

  • መሰረታዊ መረጃ። (ምን)
  • የተግባሩ ምክንያቶች ወይም ጥቅሞች። (ለምን)
  • የሚፈለገው ተግባር። (ቀጥሎ ምን)

እነዚህ ሦስቱ ክፍሎች በመፈክሩ ውስጥ በግልጽ ተለይተው መታየት የለባቸውም ነገር ግን አጠቃላይ መልእክቱ ሦስቱንም የሚያካትት መሆን አለበት። የአውስትራሊያ መንግስት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ጥሩ የጤና ልምዶችን ለማስተዋወቅ የሚከተለውን መፈክር ተጠቀመ፦ “ማድረግ እንችላለን። በጋራ የኮቪድ-19 ስርጭትን ማቆም እንችላለን።” በኮቪድ-19 ላይ ከካናዳ መንግስት ዘመቻ የነበአረው መፈክር “ሁላችንም ክትባት በመከተብ የበኩላችንን ማበርከት እንችላለን” የሚል ነበር። ህጻናት እንዲከተቡ ለማበረታታት የካናዳ መንግስት "ልጆች እንደገና ማስታወሻዎችን የሚፈጥሩበት ጊዜ አሁን ነው" የሚለውን መፈክር ተጠቅሟል። አሁን ብዙ ሰዎች ስለተከተቡ የካናዳ መንግስት የሚከተለውን ዋና መልእክት እየተጠቀመ ነው፦ "አሁን በደህና ለመኖር የሚያስችለንን ሁኔታ አመቻችተናል። ስለዚህ ጤና መርሆችን በመከተል መልካሙን ስራ እንቀጥል።"

ተናገሪ አፍሪካ፣ ካፍ፣ የአፍሪካ ሚዲያ ኤጀንሲ እና ሌሎችን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ድርጅቶች በኮቪድ-19 ወቅት “ደህንነትሽ ይጠበቅ አፍሪካ” በሚል መሪ ቃል ዘመቻ አንድ ላይ ተቀላቅለዋል። https://staysafeafrica.org/ የዘመቻው አካል በመሆን፣ የማህበራዊ ሚዲያ ሃሽታግ #ጭምብሎትንያሳዩን በመጠቀም የፊት ጭንብል በማስተዋወቅ አነስተኛ ዘመቻ አካሂደዋል።

በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በርካታ የሬዲዮ ጣቢያዎች በአንድነት ወጣቶችን በማሰባሰብ በሬዲዮ ላይ እንዲሳተፉ - የራሳቸውን የሬዲዮ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት፣ ሃሳባቸውን በአየር ላይ በማካፈል፣ ወዘተ... ዘመቻው "ዋቶቶ ሬዲዮ" https://yenkasa.org/fr/watoto-radio-une-campagne-pour-faire-entendre-les-enfants-a-lantenne/ በስዋሂሊ "የህፃናት ሬዲዮ" ማለት ነው። የህጻናትን የሬዲዮ ተደራሽነት ለማሳደግ እና ዝቅተኛ የኢንተርኔት አገልግሎት ባለባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ልጆች ድምጽ ለመስጠት ያለመ ነው።

4. ስትራቴጂ ያዳብሩ

ሀ. የመልእክት ስትራቴጂ፡ ጥሪ (መልእክት)፣ አቀራረብ (ማድረስ)፣ መልእክተኛ (ሰው)

የመልዕክት ስትራቴጂ ማዘጋጀት ያስፈልግዎታል። ቁልፍ መረጃ (ምን)፣ ለታዳሚው ያለውን ጠቀሜታ (ስለዚህ ምን) እና የድርጊት ጥሪን (ቀጥሎ ምን) ለይተዋል። አሁን ጥሪውን፣ የአቀራረብ ቃናውን፣ አቀራረቡን እና መልእክተኛውን ግምት ውስጥ ማስገባት ይችላሉ።

ጥሪው በተለያዩ አድማጮች ላይ በተሻለ ተጽእኖ የሚያሳድሩ የዋና መልእክት የተለያዩ ልዩነቶች ተብሎ ይገለጻል። አቀራረቡ ለየትኛው አድማጭ ለመድረስ የትኛውፕሮግራም እንደሚስማማ እና የትኞቹ ቅርጸቶች መልእክቱን ለማድረስ ጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገለፃል። ምን ዓይነት የአቀራረብ ቃና የተሻለ እንደሚሆን ግምት ውስጥ ማስገባት የሚችሉት እዚህ ነው። በቀልድ ማዋዛት ተገቢ ነው ወይስ ይበልጥ በቁም ነገር ብቻ ማቅረቡ ይመከራል? ወዘተ... አንዳንድ መልዕክቶች በጣም የተወሳሰቡ ከሆኑ ወይም የበለጠ ግልጽ የሆነ ውይይት የሚፈልጉ ከሆነ በዘመቻው ወቅት በተለያየ ጊዜ ረዘም ያለ ቅርጸት መጠቀም ሊኖርብዎ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ በዋናነት ግንዛቤን ማሳደግ እና ሰዎች ቁልፍ መረጃዎችን እንዲያስታውሱ ከፈለጉ፣ አጠር ያለ ወይም የበለጠ አዝናኝ ቅርጸት መምረጥ ይችላሉ።

በተጨማሪም የትኛው መልእክት ማስተላለፊያ ዋና መልዕክቶችዎን ማስተላልፍ እንዳለበት ሙከራ ማድረግ ይችላሉ። ለምሳሌ በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ ክፍለ ጊዜዎችን በማሰራጨት የትኞቹን ማሰራጫዎች እንደሚሳተፉ እና የትኞቹ እንግዶች ዋና መልዕክቶችን ማጋራት እንደሚችሉ መሞከር ይችላሉ። ከዝህም በተጨማሪ የትኞቹ ታዋቂ ሰዎች የሬዲዮ ስፖቶች ቅጂዎችን ማከናወን እንደሚችሉ ሙከራ ማድረግ ይችላሉ። ከተለያዩ አድማጮች ጋር የሚገጥሙ የተለያዩ መልእክት ማስተላለፊያዎች መጠቀሙ የበለጠ ተደማጭነት እንዲኖራቸው ያደርጋል። የኃይማኖት አባቶች በእምነት ተከታዮች ዘንድ የበለጠ ተደማጭነት ሊኖራቸው ይችላል፣ ሙዚቀኞች ወይም አትሌቶች ደግሞ በወጣቶች ላይ የበለጠ ተፅዕኖ ሊኖራቸው ይችላል። መልእክቱ መተላለፍ ያለበት ለወንዶች ወይስ ለሴቶች? ለወጣቱ ወይስ አዋቂዎች? ወዘተ...

በሚሞክሩበት ጊዜ፣ በሁሉም የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ አንዱን አካል ቋሚ ማድረጉ ጥሩ ነው። ይህ መፈክርዎ ሊሆን ይችላል፣ ይህም አድማጮች ክፍሎቹ የዘመቻው አካል መሆናቸውን እንዲያውቁት ያግዛቸዋል።

አወንታዊ አካሄድን መጠቀምም ጥሩ ነው። አወንታዊ መልእክቶች ከአሉታዊ መልዕክቶች አንጻር ሲስተያዩ የበለጠ ጠንካራ ተጽእኖ ከማድረጋቸውም በላይ እርምጃን ለመውሰድ ለማነሳሳት የተሻሉ ናቸው። ሁልጊዜ እርምጃ የመውሰድን ማበረታቻዎችን ወይም ጥቅሞችን ያሳዩ። ብዙ ማበረታቻዎች ሊኖሩ ይችላሉ፣ ስለዚህ የተለያዩ አድማጮች ከእነዚህ ማበረታቻዎች ጋር እንዴት እንደሚገናኙ ያስቡበት። መልካም ስነምግባር የሚያሳዩ ሰዎችን ታሪኮችን እንደ ማስረጃ ያካፍሉ። የመጥፎ ባህሪዎችን መዘዝ እያካፈሉ ከሆነ በአክብሮት እና አሉታዊ አመለካከቶች እንዳይቀጥሉ ተደርጎ መከናወን አለበት።

የመልእክት ስትራቴጂን ስለማዳበር ለበለጠ መረጃ ቀጣዩን ይመልከቱ፦ https://foodarc.ca/makefoodmatter/wp-content/uploads/sites/3/Develop_the_Message_Strategy.pdf

ለ. ድግግሞሽ
መደጋገም የዘመቻው አስፈላጊ አካል ሲሆን መልዕክቱ በአድማጮች አእምሮ ውስጥ መቅረቱን ለማረጋገጥ ይረዳል። በአጠቃላይ አድማጮች መልእክቱን ለማስታወስ እና እርምጃ ለመውሰድ ብዙ ጊዜ መስማት እንደሚያስፈልጋቸው ለመረዳት ተችሏል። ስንት ጊዜ መጠኑን ያለፈ መደጋገም ነው? በአንድ ክፍል ውስጥ, ምናልባት ሁለት ወይም ሶስት ጊዜዎች በቂ ናቸው፣ የአድማጮችን ትዕግሥት ሳይፈታተኑ ለማስታወስ ብቻ ነው መሆን ያለበት። ነገር ግን የሬዲዮ ስፖቶች ብዙ ጊዜ፣ በተለይም በቀን በተለያዩ ጊዜያት ሊደገሙ ይችላሉ፣ ምክንያቱም በዚህ መንገድ ለተለያዩ አድማጮች ተደራሽ ይሆናሉ!

ሐ. ቅርጸቶች
ዘመቻ ብዙ ቅርጸቶችን ሊጠቀም ይችላል። ከዚህ በታች ያሉት መረጃዎች ለዘመቻ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ አንዳንድ ቅርጸቶችን ናቸው።

ለቅርጸቶች ሙሉ ዝርዝር፣ እባክዎን ይህንን ለስርጭት ባለሙያዎች የተዘጋጀ መመሪያ ይመልከቱ፦ https://training.farmradio.fm/radio-formats/

1. የሬዲዮ ስፖቶች፣ ጂንግሎች፣ የህዝብ አገልግሎት ማስታወቂያዎች

ስፖቶች አጭር (በተለምዶ ከ15-60 ሰከንድ ርዝማኔ ያላቸው)፣ “የሚስብ” አቀራረቦች ወይም አንድ ነጠላ ግልጽ መልእክት የሚያስተላልፉ ማስታወቂያዎች ናቸው። የተለየ መልእክት ለማድረስ ውጤታማ ስለሆኑ በገበያ እና በሕዝብ አገልግሎት ማስታወቂያዎች ላይ በሰፊው ጥቅም ላይ ይውላሉ። የሬዲዮ ስፖቶች በአንፃራዊነት ርካሽ እና ለመፍጠር ቀላል ሊሆኑ ይችላሉ።

በደንብ የተሰራ ስፖት በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። በፕሮግራም ውስጥ ወይም በየፕሮግራሞች መካከል ፈጣን እረፍት በሚደረግበት ጊዜ ስፖቶቹን ማስገባት ይቻላል ። በቀን ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት የሬዲዮ ስፖትን በመድገም የተለያዩ አድማጮች በእርግጠኝነት እንዲሰሙት ማድረግ ይችላሉ። የሬዲዮ ስፖትን በበርካታ ቀናት ወይም ሳምንታት ውስጥ በመደጋገም አድማጮች መልእክቱን እንዲያስታውሱ ማድረግ ይችላሉ። አንዳንድ አድማጮች ከ10 አመት በፊት የሰሙትን ስልክ ቁጥር ወይም መፈክር ያስታውሳሉ! ለዚህም ነው የሬዲዮ ስፖቶችች የዘመቻው የጀርባ አጥንት ናቸው የሚባለው።

ዘመቻዎች አንድ የሬዲዮ ስፖት፣ ጂንግል ወይም የህዝብ አገልግሎት ማስታወቂያ ብዙ ጊዜ የሚተላለፍ ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል። ከዚህ ሌላ የዘመቻ መልእክትዎን በተለያየ ሁኔታ የሚያስተላልፉ በርካታ የሬዲዮ ስፖቶችን ማዳበር ይችላሉ።

የሬዲዮ ስፖት አዘገጃጀትን በሚመለከት ለበለጠ መረጃ የስርጭት ባለሙያ መመሪያውን ያንብቡ፦ https://training.farmradio.fm/how-to-create-radio-spots/

2. ቃለመጠይቆች፡ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል (መቼ፣ በምን ያህል ድግግሞሽ፣ ርዝመት፣ መልዕክቶች)

ቃለመጠይቆች የብዙ ፕሮግራሞች የጀርባ አጥንት ናቸው። በተለምዶ የፕሮግራሙ መሪ ጠቃሚ መረጃዎችን ወይም አስተያየቶችን ለማግኘት ለተጋባዥ እንግዳው ጥያቄዎችን ያቀርባል። ቃለ መጠይቆች በጣም ጥሩ ናቸው ምክንያቱም ሰዎች የበለጠ ዝርዝር መረጃን እንዲመረምሩ እና ሰፋ ያሉ ታሪኮችን እና ስሜቶችን እንዲያካፍሉ ይረዳሉ።

በዘመቻው ጭብጥ ላይ የተለያዩ ሰዎችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ እና ቃለመጠይቆቹን በተለያዩ ክፍሎች በማሰራጨት፣ ከተለያየ እይታ ለአድማጮችዎ የዘመቻ መልእክቶችዎን ማስተዋወቅ ይችላሉ። በጉዳዩ ላይ የተለያዩ ሰዎችን አመለካከቶች እና ታሪኮችን መስማት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ተጋባዥ እንግዶችዎ የፕሮግራሙን አድማጮች ትኩረት የሚስቡ መሆናቸውን ያረጋግጡ። በተጨማሪም ስለ ዘመቻው ጭብጥ ጠቃሚ መልዕክቶችን ያጋሩ። ለምሳሌ፦ ክትባት ላይ የመተማመን ዘመቻ አካል በማድረግ እንግዶችን ቃለ መጠይቅ እያደረጉ ከሆነ፣ እንደተከተቡ እና ሌሎች ሰዎች እንዲከተቡ እያበረታቱ እንደሆነ አስቀድመው ማወቅ አለብዎት።

የቃለ-መጠይቆች ርዝመት እንደየፕሮግራሙ አይነት ከሁለት ደቂቃ አንስቶ እስከ አንድ ሙሉ ሰዓት የሚፈጅ ሊሆን ይችላል። ሆኖም የዘመቻ አካል ሲሆኑ፣ ቃለ መጠይቁ ከዘመቻው ጭብጥ ጋር በተያያዙ በርካታ ቁልፍ ጥያቄዎች ላይ ማተኮር አለበት። ቁልፍ ጥያቄዎችን ይፃፉ፣ ነገር ግን በቃለ መጠይቁ ወቅት ተያያዥ ቀጣይ ጥያቄዎችን መጠየቁንም አይዘንጉ ምክንያቱም እንግዳው ዝርዝሮችን እንዲያብራሩ ወይም ቁልፍ ነጥቦችን እንዲያጎሉ እድሉን ስለሚፈጥር ነው።

ቃለ-መጠይቆች እንደ የዘመቻ አካል ሆነው በብዙ መንገዶች ሊያገለግሉ ይችላሉ። ዘመቻ የሚከተሉትን ሊያካትት ይችላል፦

  • የዘመቻውን ጭብጥ ለማብራራት ከተመሳሳይ ሰው ጋር ሳምንታዊ ቃለ መጠይቅ።
  • ሳምንታዊ ቃለ መጠይቅ (በተመሳሳይ ጊዜ) በተመሳሳይ ርዕስ ላይ፣ ግን በየሳምንቱ ከተለያዩ እንግዶች ጋር ማድረግ። በእያንዳንዱ ቃለ መጠይቅ ተመሳሳይ ጥያቄዎችን መጠቀም ወይም ሰዎች እውቀታቸውን እና ተለምዶዋቸውን እንዲያካፍሉ የሚያስችሉ የተለያዩ ጥያቄዎችን መጠየቅ ይችላሉ።
  • የቃለ መጠይቅ ክፍሎች በተለያዩ ፕሮግራሞች፣ ከተለያዩ እንግዶች ጋር፣ ግን በዘመቻው ርዕስ ላይ ያተኮሩ።

በቃለ መጠይቁ መግቢያ እና መደምደሚያ ላይ የፕሮግራሙ አቅራቢ የዘመቻውን ጭብጥ እና መፈክር በማጣቀስ አድማጮች ውይይቱ የዘመቻው አካል መሆኑን እንዲያውቁ ማድረግ አለበት።

የቡድን ቃለመጠይቆችም ማከናወን ይችላሉ። የፓነል ውይይቶች በርካታ እንግዶች በአንድ ክፍል ውስጥ በአንድ ርዕስ ላይ ሃሳባቸውን እንዲገልጹ ያስችላቸዋል። በፓናል ውይይቶች ወቅት የፕሮግራም አራቢው ለብዙ እንግዶች ቃለ መጠይቅ ያደርጋል። ይህ በጣም ውጤታማ የሚሆነው እንግዶቹ በተወሰነ መልኩ የተለያየ አመለካከቶች ካላቸው ወይም አስተያየታቸውን አንዳቸው ከሌላው እንዲሁም ከፕሮግራም መሪው ጋር መለዋወጥ ከቻሉ ነው። ውጤታማ የፓናል ውይይት ከቃለ መጠይቅ የየሚለየው የተለያየ የሃሳብ መንሸራሸር ስላለው ነው። እዚህ ላይ የፕሮግራም መሪው ደግሞ ከቃለ መጠይቅ አድራጊ የሚለየው አወያይ ስለሆነ ነው።

3. አሳታፊ ክፍለ ጊዜዎች

የስልክ መልእክት ወይም የጽሑፍ መልእክት አድማጮችዎን በአንድ ርዕስ ላይ ለማሳተፍ ጥሩ መንገዶች ናቸው። ስለ አንድ ርዕሰ ሃሳብ የሚሰማቸውን እንዲገነዘቡ ሊረዳቸው ይችላል። በዚህ ቅርጸት የፕሮግራም መሪው አድማጮች ደውለው ወይም አጭር የጽሁፍ መልእክት በመላክ ሃሳባቸውን በአየር ላይ እንዲገልጹ ይጋብዛል። ይህ ውጤታማ ሆኖ የሚሰራው የፕሮግራም መሪው ርዕሱን ከዘመቻው መልእክቶች ጋር በተዛመደ መልኩ ሲቀርጽ ነው።

ይህ በዘመቻ ውስጥ ውጤታማ ቅርጸት ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን ተግዳሮቶችንም ሊያስከስት ይችላል። አድማጮችዎ በዘመቻው መልእክቶች የሚስማሙ ከሆነ፣ ይህ ቅርጸት የዘመቻ መልእክቶችዎን በአድማጮችዎ በኩል ያጠናክራል ማለት ነው። ሆኖም፣ አንዳንድ አድማጮች በመልእክቶችህ ላይስማሙ ይችላሉ። የአድማጮችዎን አስተያየት ያክብሩ እና ለጊዜያቸው ያመስግኗቸው ምክንያቱም በዘመቻው የሚፈለጉትን እርምጃዎች ከመውሰድ የሚያግዷቸውን እንቅፋቶችን እየገለጹ ሊሆን ስለሚችል። እነዚህን መሰናክሎች በአክብሮት ለመፍታት እና የአድማጮቹ ስጋት ቢኖርም የሚመረጠው አጠቃላይ አካሄድ በዘመቻው የተጠቆመውን እርምጃ (ለምሳሌ በተሳሳተ መረጃ የሚሰራጩ ፍራቻዎች ቢኖሩም ክትባት መውሰድ) እንዴት እንደሆነ ለማሳየት የባለሙያ እንግዳ ይዘው ይቅረቡ። የአድማጮችን ስጋት ያለአግባብ አያቅልሉባቸው።

ቮክስ ፖፕስ አድማጮች ከዘመቻው መልእክት ጋር እንዲሳተፉ እና በርዕሱ ላይ የራሳቸውን ልምዶች ወይም አመለካከቶች እንዲያካፍሉ የሚያስችል ሌላ ቅርጸት ነው። አንዳንድ ቮክስ ፖፕስ የተለመዱ ስጋቶችን ወይም አለመግባባቶችን ሊያጋሩ ይችላሉ። እነዚያን ስጋቶች ወዲያውኑ ለመፍታት የሚያስችል ባለሙያ መኖሩ ዘመቻዎን ያጠናክራል። የድምጽ ክሊፖችን ሲያስተዋውቁ ለአድማጮችዎ የአድማጮች ድምፅ ናሙና መሆናቸውን መንገሩን ያስታውሱ። ሁሉም ሰው በዚህም ሆነ በዚያ የሚያስበው ይህን ነው ብለው እንዳይናገሩ። በዘመቻው መልእክቶች የሚስማሙ ሰዎችን ድምጽ ብቻ ካካተቱ፣ ለአድማጮች ሊያጠራጥራቸው ይችላል። የሚስማሙ ድምጾች ብቻ በአየር ላይ እንደሚሰሙ ካወቁ ላያዳምጡ ወይም ላያምኑ ይችላሉ።

4. አዝናኝ ክፍለ ጊዜዎች

የዘመቻ መልዕክቶችን ለማጋራት ዘፈኖች እንዲሁ አስደሳች መንገድ ሊሆኑ ይችላሉ። ዘፈኖች ልዩነትን እና መዝናኛን ያካትታሉ፣ የአድማጮችን ባህል ያንፀባርቃሉ፣ በመልካም ስሜት የተሞላ ምላሽን ያበረታታሉ እንዲሁም አድማጮች ውስብስብ መረጃዎችን እንዲያስታውሱ ያግዛሉ። ግጥሞች በዚህ መንገድ ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ።

ድራማዎች የአድማጮችን ሀሳብ ለመቅረጽ እና እርምጃ እንዲወስዱ ለማበረታታት ውጤታማ መንገዶች ናቸው። ለዚህም ነው ብዙ ማስታወቂያዎች ታሪክ የሚናገሩት። በባለ አንድ ክፍል ሆነ ተከታታይ ድራማ ለዘመቻ ለመስራት በጣም ውድ ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን ከ2-5 ገፀ-ባህሪያት ያላቸው አጫጭር ድራማዎች ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፣ ወይም ሚኒ ድራማ ተከታታይ አጭር (ከ2-5 ደቂቃ ርዝመት ያለው) ታሪክን የሚያስተዋውቅ ወይም ታሪክን የሚያሳዩ ናቸው። ሕያው ወይም አስቂኝ ውይይት ጋር የገጸ ባህሪ ልምድ። ድራማ በብዙ የሬዲዮ ስፖቶች ውስጥም ቁልፍ አካል ነው።

ጥያቄዎች ወይም ውድድሮች ላይ አድማጮችዎን የሚያሳትፉበት እና ከዘመቻዎ ጋር የተያያዙ ጠቃሚ መረጃዎችን መቀበላቸውን ለማረጋገጥ ሌላ አስተማማኝ መንገድ ናቸው። ባካፈልዋቸው ቁልፍ መረጃዎች ላይ መጠየቅ እና አድማጮችዎ ከዘመቻ መልእክቶች ጋር የተያያዙ መፈክሮችን፣ ዘፈኖችን ወይም ግጥሞችን እንዲያቀርቡ ማድረግ ይችላሉ።

5. ሌሎች ክፍለ ጊዜዎች

የሚጋራ ትክክለኛ መረጃ ካለ በዘመቻ ውስጥ የተካተተ ዝርዝር ወይም ነጠላ ንግግር አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ብዙ ጊዜ፣ አድማጮች በዘመቻ ግብዎት ላይ እርምጃ እንዲወስዱ እንደዚህ አይነት ትክክለኛ መረጃ አስፈላጊ ነው! ክትባትን ለማስተዋወቅ በሚደረግ ዘመቻ፣ ይህ አድማጮች የሚከተቡባቸው ክሊኒኮች፣ ቀኖች፣ ሰአቶች እና ቦታዎች ሊያካትት ይችላል። ዝርዝሩን በበርካታ ፕሮግራሞች ላይ በግልፅ በማንበብ በተቻለ መጠን ብዙ አድማጮች ይህን ጠቃሚ መረጃ እርምጃ እንዲወስዱ ማድረግ ይችላሉ።

ፕሮግራም መሪ የሚያቀርበው መጣጥፍ ወይም ማስታወሻ የራሱ የፕሮግራም መሪውን ሆነ የሌላ ሰውን የቅርብ ጉዳይ ለመጋራት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ሁለቱም ምንም አይነት አማላጅ ወይም ቃለ መጠይቅ ጠያቂ ሳይኖራቸው ስለራሳቸው ልምድ እንዲናገሩ እድሉን ይሰጣሉ። ይህ ክፍል በተለምዶ ከ5-7 ደቂቃ የሚወስድና ወጣ ያለ ልምድን ወይም የህይወት ታሪክን ያካፍላል። ይህንን ክፍለ ጊዜ በሚያዘጋጁበት ጊዜ ከፕሮግራም አዘጋጁ ጋር ወይም ከማስታወሻ ጽሁፍ ያዡ ጋር በመተባበር የግል ታሪካቸውን እና እንዴት ሊተርኩት እንደሚችሉ ማሰቡ አስፈላጊ ነው። የክትባት ዘመቻ ጋር በተያያዘ ማስታወሻው በህመም የተሠቃየውን ሰው ተሞክሮ ለማካፈል እንዲሁም ሌሎች በክትባት በሽታውን ሊከላከሉ እንደሚችሉ ለማበረታታት ውጤታማ መንገድ ሊሆን ይችላል። የፕሮግራም መሪው መጣጥፍ በተመሳሳይ ሁኔታ ስለበሽታው ያለውን ልምድ ወይም ክትባት ለመውሰድ ውሳኔ በማካፈል አበረታች ሊሆን ይችላል።

መ. ከማህበራዊ ሚዲያ ጋር ውህደት/መመሳሰል

በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ንቁ መሆን የዘመቻ መልእክትዎ ብዙ ሰዎችን በብዛት መድረሱን ለማረጋገጥ ጥሩ መንገድ ነው። የዘመቻ መልእክትዎን በዋትስአፕ፣ ፌስቡክ ወይም ትዊተር በኩል ለአድማጮች ያካፍሉ። ይህን ለማድረግ ቀላሉ መንገድ የሬዲዮ ስፖትዎችዎን ወይም መፈክርዎን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ፣ ምናልባትም በምስል ማጋራት ነው። ምስሉ የዘመቻ አዶውን እና የጣቢያውን አርማ የሚያጣምር ግራፊክስ ወይም መፈክርዎ (አጭር ከሆነ) በጽሁፍ ሊሆን ይችላል። ከዘመቻዎ ጋር የተያያዘ ጠቃሚ ቃለ ምልልስ ለመስማት ሰዎች በትክክለኛው ጊዜ እንዲታደሙ ለማበረታታት ማህበራዊ ሚዲያ ጥሩ መንገድ ነው፣ ስለዚህ እነዚህን ቃለመጠይቆች ማስተዋወቅዎን አይርሱ! በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከቁልፍ የዘመቻ ቃለመጠይቆች የተቀነጨቡትን ማጋራት ይችላሉ። በመጨረሻም፣ አድማጮችዎ እርምጃ እንዲወስዱ የሚያግዝ ቁልፍ መረጃ ካሎት፣ ለምሳሌ፣ እንደ ክትባት የሚሰጡ ክሊኒኮች፣ ቀን እና ቦታ፣ ያሉትን መረጃ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በማጋራት ለሰዎች በማንኛውም ጊዜ ተደራሽ እንዲሆን ያድርጉ። በተጨማሪም አድማጮችዎ በፌስቡክ ገፅዎ ላይ ክትባቱን እየሰጡ ያሉ ክሊኒኮችን ሙሉ ዝርዝር ቀኖች እና ቦታዎች ማግኘት እንደሚችሉ በአየር ላይ ማሳወቅ ይኖርብዎታል። ይህ በአየር ላይ የሚያጋሯቸውን ሁሉንም መረጃዎች ለማስታወስ የሚያስፈልግዎትን ጥረት ይቀንሳል።

ሠ. በዘመቻ ውስጥ ብዙ ፕሮግራሞችን መጠቀም

ሁሉም አድማጮችዎ የዘመቻውን መልእክት እንዲሰሙ በሬዲዮ ጣቢያዎ ውስጥ በርካታ ፕሮግራሞችን መጠቀሙ ሊጠቅም ይችላል። ሁሉም ፕሮግራሞች የዘመቻውን ርዕስ የሚያካትቱ ከሆነ አድማጮችዎ ወጥ የሆነ ድምጽ እና መፈክር በመጠቀም ዘመቻውን እንዲያውቁ ለማድረግ ይሞክሩ።

ለተለያዩ ፕሮግራሞች ክፍለ ጊዜዎችን ሲነድፉ ስለ አድማጮች፣ መልእክቱ፣ መልዕክቱን ማድረስ እና መልእክት ማስተላለፊያውን ማጤኑን አይዘንጉ።

በኮቪድ-19 ክትባት ዙሪያ እምነት እንዲኖር በሚደረገው ዘመቻ ውስጥ የተለያዩ የሬዲዮ ፕሮግራሞች እንዴት እንደሚካተቱ አንዳንድ ምሳሌዎች እነሆ።

ጤና ላይ የሚያተኩር የሬድዮ ፕሮግራም ካለዎት...

ታዳሚዎችዎ እንዲከተቡ ለማበረታታት የፋርም ሬዲዮ ኢንተርናሽናል የሬዲዮ ምንጮችን በኮቪድ-19፣ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ሰነዶች እና ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተገኘውን ተግባራዊ መረጃ መጠቀም ይችላሉ። ይህ መረጃ በእያንዳንዱ የጤና ፕሮግራም ወቅት በሚተላለፉ የሬዲዮ ስፖቶች ላይ ወይም እንደ መደበኛ "ጠቃሚ ምክሮች" ክፍለ ጊዜ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ከጤና ባለሙያዎች ጋር የተደረጉ ቃለ-መጠይቆችን ማካተት ይችላሉ። ከነዚህም ውስጥ በተከተቡ እና ባልተከተቡ ሰዎች መሃል በሽታው ከሚያደርገው ጫና ልዩነት፣ ስለ ኮቪድ-19 ክትባት የተለመዱ ጥያቄዎች ወይም ስጋቶች፣ እና የኮቪድ-19 ክትባትን እንዴት ማግኘት እንደሚቻል የሚሉት ይገኙበታል። በተጨማሪም ሙሉ ለሙሉ የተከተቡ ሰዎች ለምን እንደተከተቡ ወይም ከክትባት በኋላ በኮቪድ-19 ዙሪያ ስላላቸው ልምድ ቃለ መጠይቅ ማድረግ ይችላሉ።

በትምህርት ላይ የሚያተኩር የሬዲዮ ፕሮግራም ካለዎት…

አንድ ሰው ትምህርት ለመከታተል ጤናማ መሆን እንዳለበት የሚለውን እውነታ ማጉላት ይችላሉ። ተማሪዎችን እና መምህራንን ደህንነታቸውን ለመጠበቅ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ባሉ ህጎች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቃለ-መጠይቆችን ያቅዱ፣ ወይም ወረርሽኝ በሚከሰትበት ጊዜ ትምህርት ለመቀጠል የሚያስችል እቅድን የሚዳስስ ቃለ መጠይቅ ያከናውኑ። መምህራን እና ተማሪዎች የኮቪድ-19 ክትባቶችን እንዲያገኙ የትምህርት ሚኒስቴር ባለስልጣናት እቅዶቻቸውን እንዲያካፍሉ መጠየቅ ይችላሉ። እንዲሁም ከተማሪዎች እና አስተማሪዎች ጋር ክትባቱን ይከተላሉ ወይስ አይከተቡም፣ ለምን ሊከተቡ እንደወሰኑ የሚሉት ርዕሶች ዙሪያ ቃለ-መጠይቆችን ማድረግ ። ብዙ ተማሪዎች ስለመከተብ የሚያቅማሙ ከሆነ፣ ይህ ክፍለ ጊዜ የተማሪዎችን ስጋት ከሚፈታ የጤና ወይም የትምህርት ባለስልጣን ጋር ቃለ መጠይቅ ሊደረግበት ይችላል።

የስፖርት ሬዲዮ ፕሮግራም ካለዎት…

ለጠንካራ አትሌቶች ጥሩ ጤና ያለውን ጠቀሜታ እና የኮቪድ-19 ክትባት ጥሩ ጤናን እንደሚደግፍ አጽንኦት ሰጥተው መናገር ይችላሉ። የፕሮግራም አወጣጥዎ ሙሉ በሙሉ ከተከተቡ የሀገር ውስጥ አትሌቶች ጋር ቃለ-መጠይቆችን እና ምስክርነቶችን ሊያካትት ይችላል በተጨማሪም አድማጮች ጥሩ ጤናን ለመደገፍ ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ ያሳስባል። ኮቪድ-19 ይዞት ከሚያውቅ አትሌት ጋርም ቃለ መጠይቅ ማድረግ እና በሽታው በስፖርታዊ ስልጠና እና ጤና ላይ ስላለው ዘላቂ ተጽእኖ መወያየት ይችላሉ። እንዲሁም ሙሉ በሙሉ የተከተቡ ታዋቂ አትሌቶች አድማጮች እንዲከተቡ እና ከኮቪድ-19 ሊመጣ ስለሚችል ሆስፒታል ከመጨነቅ ነጻ የሆነ ጤናማ፣ ስፖርት እንዲኖሩ የሚያሳስቡበት የሬዲዮ ስፖቶችን እና ጂንግልስ ማዘጋጀት ይችላሉ። አትሌቶች እና ደጋፊዎቻቸው መከተብ እንዲችሉ በዕቅዳቸው ላይ ለመወያየት ከስፖርት እና ከሀገር አቀፍ የስፖርት አካላት ጋር የሚመለከተውን ቃለ መጠይቅ ማዘጋጀትም ይቻላል። በተጨማሪም፣ እንደ ጭንብል ስለማድረግ ያሉ ጤናን መጠበቂያ እርምጃዎችን ስለመከተል ቮክስ ፖፕዎችን ወይም በአካባቢው ስፖርታዊ ግጥሚያ ላይ ከሚገኙ አድናቂዎች ጋር ቃለ መጠይቅ ማድረግ ይችላሉ።

የፖለቲካ ሬድዮ ፕሮግራም ካለዎት…

የፖለቲካ የሬድዮ ፕሮግራሞች ክትባቱን ለመውሰድ መወሰናቸውን እና የክትባት ልምዳቸውን የሚያብራሩ የሀገር ውስጥ የፖለቲካ መሪዎችን ድምጽ (የበለጠ ተጽእኖ ስላላቸው) ማቅረብ አለባቸው። የአድማጮችዎን ፍላጎት ለማሟላት ሁለቱንም ገዥ እና ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን አቅርቡ። ይህ በተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ውስጥ በሽፋን አካባቢዎ ውስጥ ከፍተኛውን የአድማጮች ቁጥር እንዲያገኙ ያደርጋል። እነዚህን መልዕክቶች ለማስተላለፍ ቃለመጠይቆች ወይም የሬዲዮ ስፖቶችች ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።

የፖለቲካ ፕሮግራሞች ብዙ ተመልካቾችን ይደርሳሉ ስለዚህ ስለ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሌላ አስፈላጊ ገጽታ ለመወያየት ጥሩ ቦታ ሊሆኑ ይችላሉ፦ የሃሰት ዜናንም አስመልክቶ ዳሰሳ ማድረግ። ስለ ክትባቱ የተለያዩ የተሳሳቱ አመለካከቶች የጤና ባለሙያዎችን ቃለ መጠይቅ ያድርጉ። ይህ "የሳምንቱን አፈ ታሪኮች" ወይም የአንድ ጊዜ ፕሮግራም ወይም መደበኛ ክፍለ ጊዜ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም የተሳሳተ መረጃ እንዴት ወይም ለምን እንደሚሰራጭ እና በፖለቲካ ወይም በሌሎች ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ስላለው ተጽእኖ ከባለሙያዎች ጋር ቃለ መጠይቅ ማድረግንም ያስቡበት።

የመዝናኛ ሬዲዮ ፕሮግራም ካለዎት…

የመዝናኛ የሬዲዮ ፕሮግራሞች ሙዚቃ እና ሙዚቀኞች፣ ድራማ እና የድራማ ባለሞያዎች፣ ገጣሚዎች እና ሌሎችንም ያካትታሉ። ታዋቂ አርቲስቶች ስለ ክትባቶች አስፈላጊነት፣ ከተከተቡ በኋላ ስላላቸው ልምድ እና በአጠቃላይ የኮቪድ-19 ክትባቶችን ለማስተዋወቅ እንዲናገሩ ለማድረግ ይሞክሩ። የእነሱ ተደማጭነት በአድማጮችዎ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ይህ በስፖቶች፣ በቃለ መጠይቆች፣ በሙዚቃ፣ በግጥሞች፣ በድራማዎች ወይም በሌላ በማንኛውም መልኩ ሊከናወን ይችላል። የአርቲስቶቹ አድናቂዎች በሚያዳምጡበት ጊዜ እነዚህ ክፍለ ጊዜዎች በሌሎች ፕሮግራሞች ላይ ሊካተቱ ይችላሉ። ይህ ሬዲዮ ጣቢያው የአዝናኞችን ፈጠራ ሙሉ በሙሉ መጠቀሙን ያረጋግጣል።

ለምሳሌ በማላዊ፣ ሙዚቀኞች ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዙ ጉዳዮች፣ እጅ መታጠብን፣ አካላዊ ርቀትን፣ አፍና አፍንጫን በጭምብል መሸፈን እና ሌሎች ቅድመ ጥንቃቄዎችን ጨምሮ ዘፈኖችን አዘጋጅተዋል። እነዚህን አስቀድመው የተዘጋጁ ፕሮግራሞችን ከመጠቀም በተጨማሪ አንዳንድ አዝናኝ ሰዎችን ስለክትባት ልምዶቻቸው በግል ደረጃ በማነጋገር ሌሎች እንዲከተቡ ማበረታታትዎን ያረጋግጡ።

የሀይማኖት የሬዲዮ ፕሮግራም ካለዎት…

ከፈጣሪ ፍላጎቶች ውስጥ እንደ አንዱ የመኖር እና ጤናማ የመሆንን አስፈላጊነት መሆኑን ይናገሩ። ክትባቱን የወሰዱ እና ተከታዮቻቸውም እንዲከተቡ የሚያበረታቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሃይማኖት መሪዎችን በጣቢያው አካባቢ ይፈልጉ። በክትባቱ ላይ ስላላቸው እምነት እና በስራ ቦታቸው ማህበረሰቡን በስነ-ስርአት ወቅት ደህንነትን ለመጠበቅ ስላላቸው እቅድ ቃለ መጠይቅ ማድረግ ትችላለህ። ከተቻለ የኮቪድ-19 ክትባት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አውሬ ነው (666) የሚሉ ወሬዎችን እና የተሳሳቱ መረጃዎችን ማስወገድ ይችላሉ። የሃይማኖት መሪዎችን በሬዲዮ ቦታዎች ያሳዩ እና ከሁሉም ሀይማኖቶች እና ቤተ እምነቶች የተውጣጡ መሪዎችን በሬዲዮዎ መገኛ አካባቢ መጠቀማቸውን ያረጋግጡ። እያንዳንዱ አድማጭ ከሃይማኖት መሪዎቻቸው መልእክቱን እንዲቀበል ለእያንዳንዱ ሃይማኖት / ቤተ እምነት እድል መስጠት አስፈላጊ ነው፣ ብዙዎች ከሌላ ሀይማኖት/የሃይማኖት መሪ የሚመጣን መልእክት በቁም ነገር ላያዩት ይችላሉ።

በሃሰተኛ ዜና ላይ የሚያተኩር የሬዲዮ ፕሮግራም ካለዎት…

አንዳንድ የሬዲዮ ጣቢያዎች ስለ ትክክለኛ መረጃ አድማጮቻቸውን የሚያሳውቁ የሃሰተኛ ዜናዎች ላይ ልዩ ፕሮግራሞች አሏቸው። እንደዚህ አይነት ፕሮግራም ካለዎት ስለ ኮቪድ-19 በአጠቃላይ እና ስለ ክትባቱ የተሳሳቱ መረጃዎችን መፍታት ይችላሉ። ሃሰተኛ ወሬዎችን ለማስወገድ እና በትክክለኛ መረጃ ለመተካት የቃለ መጠይቅ ባለሙያዎችን ማካተት ይችላሉ። ስለ ኮቪድ-19 ክትባት አንዳንድ ታዋቂ አፈ ታሪኮች የአውሬው ምልክት ነው (666) ወይም ክትባት ሲወስዱ መካን ይሆናሉ የሚሉት ይገኙበታል። እነዚህን ወሬዎች ለማስወገድ ከሁሉ የተሻለውን መንገድ አስቡበት። ምናልባት የጤና ኤክስፐርት ትክክለኛ መረጃ ይሰጡ ይሆናል ነገር ግን የሃይማኖት መሪዎች "666" የተባለውን አሉባልታ ለማጥፋት የተሻለ አቋም ሊኖራቸው ይችላል፣ ሙሉ በሙሉ የተከተቡ ሰዎች ግን በቅርብ ጊዜ መንትዮች እንኳን ሳይቀር ልጅ እንደወለዱ መወያየት ይችላሉ!

ለወጣቶች ፕሮግራም ካለዎት…

ክትባቱን ለመውሰድ በሚመለከት ስለወሰዱት ውሳኔ እና ለሌሎች ወጣቶች የሚያስተላልፉትን መልእክት በተመለከተ ከወጣቶች ጋር ቃለ-መጠይቆችን ማካተት ይችላሉ። አንዳንድ ወጣቶች ክትባቱን በተመለከተ፣ ደህንነቱን፣ ስለ መዋለድ፣ ክትባቱ በመጀመሪያ ለአዋቂዎች ብቻ ይሰጥ ስለነበር ማመንታት ሊታይባቸው ይችላል። እነዚህን ስጋቶች በቃለ መጠይቅ መፍታት። እንዲሁም ተደማጭነት ያላቸውን ሰዎች-የማህበረሰብ መሪዎችን፣ የወጣት አክቲቪስቶችን፣ ሙዚቀኞችን ወይም ሌሎች ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን በመጠቀም የሬዲዮ ስፖቶችን መጠቀም ይችላሉ። ድራማ እና ሙዚቃ ወጣቶች እንዲከተቡ ለማበረታታት ጥሩ መንገድ ናቸው። በተጨማሪም ውድድሮች ወይም ጥያቄዎች ወጣቶችን በርዕሱ ላይ ለማሳተፍ ያላቸውን ፍላጎት ከመጨመሩ ረገድ ጥሩ አስተዋጾኦ ያበረክታሉ። ወጣቶች ስለ ኮቪድ-19 ክትባት ወደ ጣቢያውን በመደወል ግጥም እንዲያካፍሉ ወይም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ እንዲያጋሩ ያበረታቱ።

ለሴቶች የሚሆን ፕሮግራም ካለዎት…

የሴቶች ፕሮግራምዎ ስለ ኮቪድ-19 ክትባት እና ሌሎች የጤና እርምጃዎች የሴቶችን ልዩ ስጋት ለመፍታት ጥሩ መድረክ ሊሆን ይችላል። ሴቶች ለመከተብ ተጨማሪ እንቅፋት ሊያጋጥሟቸው ወይም የተለያዩ ስጋቶች ሊኖራቸው ይችላል። የጥሪ ፕሮግራም ወይም ከባለሙያ እንግዶች ጋር የሚደረግ ቃለ ምልልስ እነዚህን ስጋቶች ለመፍታት ይረዳል። የሬዲዮ ስፖቶች፣ ሙዚቃ ወይም ድራማ የዘመቻዎትን ቁልፍ መልዕክቶች ለማጋራት አዝናኝ መንገዶች ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህ ተመልካች ላይ ተፅዕኖ ሊኖራቸው ስለሚችሉ ሴት መሪዎችን ከግምት ያስገቡ።

እንደተመለከቱት፣ በሬዲዮ ጣቢያዎ ውስጥ ብዙ ፕሮግራሞችን፣ ቅርጸቶችን እና ድምጾችን በመጠቀም ሁሉም አድማጮችዎ የዘመቻ መልዕክቶችን የመስማት እድል ያገኛሉ። ዘመቻ ፈጠራን የሚያበረታታ መልካም ዕድል ነው። ነገር ግን፣ በተለይም የቃለ መጠይቅ ክፍለ ጊዜዎችን ሲያስተዋውቁ እና ሲጨርሱ የጋራ መፈክር እና/ወይም መግቢያ እና የመለያ ዜማ መጠቀምዎትን እንዳይዘነጉ።

ለምሳሌ፦ በኮቪድ-19 የክትባት እምነት ዘመቻ፣ በሁሉም ፕሮግራሞች እና ከሁሉም እንግዶች ጋር፣ “ዛሬ [ከክትባት ጋር በተያያዘ ጉዳይ] ከ[የእንግዳው ስም] ጋር ቃለ መጠይቅ አለን።” [የኛ ጣቢያ] ዘመቻ ሁሉም አድማጮቻችን እራሳቸውን ከኮቪድ - 19 በክትባት እንዲከላከሉ ለማበረታታት ነው። እንደተከተቡ ተስፋ እናደርጋለን ያልተከተቡ ከሆነ ደግሞ ክትባቱን ለማግኘት በአካባቢያችሁ የሚገኘውን ጤና ጣቢያን እንደሚጎበኙ ተስፋ እናደርጋለን። በመቀጠል የማስተዋውቃችሁ…”

5. በዚህ አይነት ዘመቻ ወቅት መደረግ ያለባቸው እና መደረግ የሌለባቸው

በዘመቻ መደረግ ያለባቸው

በዚህ ሰነድ ውስጥ አብዛኛዎቹን የዘመቻ ስራዎች ሸፍነናል። እዚህ ደግሞ ልብ ለባሉ ያሚገባቸው ናቸው።

ቻናሎችን እና አቀራረቦችን ያጣምሩ፡ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ አድማጮች ላይ ለማነጣጠር የተለያዩ የመገናኛ መንገዶችን፣ ቴክኒኮችን እና መሳሪያዎችን ያጣምሩ። በተለያዩ ቅርፀቶች የሚተላለፉ የሬዲዮ መልእክቶች ከግለሰባዊ ጣልቃገብነት ጋር ሲጣመሩ የባህሪ ለውጥን የመፍጠር እድላቸው ሰፊ። ለምሳሌ ከአብያተ ክርስቲያናት ወይም መስጊዶች የአምልኮ ስፍራዎች፣ ከማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ከጤና አቅራቢዎች እና ከትምህርት ቤቶች።

አዳዲስ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችን ይጠቀሙ፦ ቴክኖሎጂ በየጊዜው ይዘምናል፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መከታተል አስፈላጊ ነው። በይነመረብ እና ሌሎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ማህበራዊ ሚዲያ አውታረ መረቦች ፣ በነመረብ ላይ የሚከናወኑ የስብሰባ አውታሮች፣ ዩትዩብ ፣ የጽሑፍ መልእክት፣ ስካይፕ ወዘተ... እንዴት እንደሚሰሩ እራስዎን ማወቅ፣ ለብዙ ተመልካቾች መልዕክቶችን በፍጥነት ለማስተላለፍ ያላቸውን አቅም መጠቀም እና ለፈጣን እርምጃ መንቀሳቀስ ለዘመቻ ትልቅ ጥቅም አለው።

ቅድመ-ሙከራ፡- ግብዓቶቹ የታሰበውን ውጤት እንዲያመጡ በምክክር፣ በትኩረት ቡድኖች፣ በአስተያየት ክፍለ-ጊዜዎች እና በመሳሰሉት ከባለድርሻ አካላት፣ አጋሮች እና የታለመላቸው ታዳሚዎች ጋር ሁሉንም የመልእክት እና መገናኛዎች ደጋግመው ይፈትሹ። ሌሎች ዘመቻዎች እና ተመሳሳይ ኢላማ ውስጥ ያሉ ታዳሚዎች እንዴት እዚህ እንደደረሱ ጥናት ያደርጉ። ዘመቻዎቹ የተሳካላቸው አካላት እንዴት እንደተሳካላቸው ካወቁ በኋላ ራሱን መተግበሩ ጥሩ ነው።

ቀጥተኛ እና ግልጽ ይሁኑ፦ ግልጽ የሆነ ተግባር የሚጠይቅ ቀጥተኛ መልእክት ከተወሳሰቡ እና ከበርካታ መልእክቶች የበለጠ ለመረዳት ቀላል ናቸው።

የዘመቻ ግብዎን ለማሳካት የባለድርሻ አካላት እና ታዳሚዎች ነባራዊ ጥረቶች ዋጋ በዘላቂነት፦ በዘመቻዎ እነዚህን ጥረቶች ማብዛት ወይም ማጎልበት እንደሚችሉ ያሳዩ። ባለድርሻ አካላት እና ኢላማ የተደረጉ አድማጮች ግባቸው ላይ እንዲደርሱ ያግዟቸው። ከባለድርሻ አካላት ድጋፍን ለማረጋገጥ የተመረጠው መንገድ ዘመቻዎ ግባቸውን እንዲያሳኩ መርዳት ነው።

ላልተጠበቀ ነገር ሁሌም ዝግጁ ይሁኑ፦ በዘመቻው ወቅት የአካባቢዎን አሉታዊም ይሁን አወንታዊ ጣልቃገብነት ተፅእኖ በየጊዜው ይከታተሉ። በዚሁ መሠረት ማስተካከያ ለማድረግ ዝግጁ ይሁኑ። ማንኛቸውም ያልተጠበቁ ክስተቶች ለማስተናገድ ወይም ቀውሶችን ለማቃለል ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ መልእክት ማስጀመር አለባቸው። የግንኙነት ስልቱ በዝግጅት ደረጃ ሊከሰቱ የሚችሉ ያልተጠበቁ ሁኔታዎችን መዘርዘር እና ቆራጥ ምላሽ ለመስጠት አግባብነት ያላቸውን የድርጊት መርሃ ግብሮችን መፍጠር አለባቸው።

ስነምግባር አክብሮ፡ መልእክቶች እና አሰራሮቻቸው ለስርዓተ-ፆታ እና ከሰብአዊ መብቶች ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን ያረጋግጡ። የዘመቻ መልእክቶች ስለሴቶች እና ወንዶች እና ስለ ሚናዎቻቸው አሉታዊ አመለካከቶችን ከማጠናከር መቆጠብ አለባቸው። የእርስዎን የግንኙነት ስትራቴጂ በማቀድ እና በዘመቻ ዝግጅቶች ውስጥ እንዲሳተፉ (ለምሳሌ አስፈላጊ ከሆነ የምልክት ቋንቋ ትርጉም በመስጠት) በማሳተፍ ብዙ መድልዎ በሚደርስባቸው (ለምሳሌ በፆታ፣ አካል ጉዳተኝነት፣ ዕድሜ፣ ሃይማኖት ወይም ጎሳ ምክንያት) በሚያጋጥሟቸው ስጋቶች ላይ ያተኩሩ።

በዘመቻ መደረግ የሌለባቸው

የበለጠ ትኩረት ለማግኘት ብለው የስርዓተ-ፆታ ጉዳዮችን ወይም የስነ-ምግባር መርሆዎችን ከመተው ይቆጠቡ። ለምሳሌ፦ ለባህል የማይነቃነቅ ቋንቋ ከመጠቀም ወይም ስሜት ቀስቃሽ ምስሎችን ከማሳየት ይቆጠቡ።

ሆን ተብሎም ሆነ ባለማወቅ በርካታ አድልዎችን እያስተናገዱ ያሉ ሰዎችን ከዘመቻ እንቅስቃሴዎች አታግዱ። ለምሳሌ ዘመቻው ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለማስቆም ከሆነ ድርጊቱን የሚፈጽሙትን ከመግፋት ይልቅ እንደ የመፍትሄው አካል የሚያካትቱበትን መንገድ ይፈልጉ።

በአንድ የህብረተሰብ ክፍል ላይ የጥላቻ ወይም የጥቃት አቋም ከመውሰድ ይቆጠቡ፣ ለምሳሌ ሁሉንም ሀይማኖቶች ኮቪድ-19 ክትባት ላይ ለሚስተዋለው ማመንታት ተጠያቂ በማድረግ፣ ወይም የዘመቻውን አላማ ለማሳካት የሚሰሩትን የሌሎችን ስራ በማጥላላት ጥረቶችዎን ስኬታማ ያረጋቸዋል ማለት ኣይደለም። ይልቁንስ የሌሎችን ልምድ ይገንቡ እና ያሉትን ጥረቶች ለማሻሻል እና የተሳሳቱ እርምጃዎችን ለማስተካከል ገንቢ አካሄዶችን ይፈልጉ።

በመደለያዎች አይዘናጉ። የመገናኛ ቻናል ወይም የኮምዩኒኬሽን መሳሪያ ማራኪ መስሎ ስለታየ ብቻ (ለምሳሌ፣ የሬዲዮ ጂንግል፣ አጭር የጽሁፍ መልዕክት ዘመቻ፣ ወይም ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ለገበያ ለማቅረብ ነፃ ዘመቻ ለማድረግ የሚያቀርቡት ፕሮፖዛል) ለእርስዎ የተለየ ዘመቻ ተገቢ ነው ማለት አይደለም። ከልክ ያለፈ የኮምዩኒኬሽን እንቅስቃሴዎች አንዳንድ ጊዜ ወደ ኋላ የመመለስ፣ ትኩረትን የመከፋፈል ወይም ኢላማ የተደረጉ አድማጮችን ከዋናው መልእክትዎ ሊያርቁ ይችላሉ። የተለያዩ ቻናሎች ጥቅማጥቅሞችን እና መዘዞችን መመርመር በጣም አስፈላጊ ነው። እነዚህ በእርስዎ አውድ ውስጥ ስለሚሰሩ ይጠቀማሉ።

ጋዜጠኞች እና የስርጭት ባለሙያዎች ለተለያዩ አስተያየቶች እና የተለያዩ ቡድኖች ምን ያህል የአየር ሰዓት እንደሚሰጡ ትክክለኛ ውሳኔዎችን መወሰናቸው አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ፣ ሁሉም ሰው የራሱን አስተያየት የማመን መብት ቢኖረውም እንደ የአየር ንብረት ለውጥ ባሉ ሳይንሳዊ ጉዳዮች፣ ህጋዊ የአየር ንብረት ሳይንቲስቶች አስተያየት የበለጠ ክብደት ስላላቸው እርስዎም በስርጭት ጣቢያዎ ማንጸባረክ ያለብዎት የነዚህኑ የሳይንቲስቶች አስተያየት ነው።

በመንደርዎ፣ በከተማዎ፣ ወይም በክልልዎ ምን እየተደረገ እንዳለ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት ህዝቡ እንደ እርስዎ ባሉ የስርጭት ባለሙያዎች እምነቱን ይጥላል። ስለዚህ ስለ አንድ ታሪክ ከመዘገብዎ በፊት ጊዜ ወስዶ እውነታውን መሰብሰብ የእርስዎ ኃላፊነት ነው። ያለበለዚያ፣ አድማጮችዎ ተዓማኒነቱ በጣም አነስተኛ ወደ ሆነ የአካባቢ እውቀት ወደሌለው ምንጭ ሊዞሩ ይችላሉ፣ ይህ ደግሞ የተሳሳተ መረጃ እንዲሰጣቸው ሊያደርጋቸው ይችላል።

በዚህ ላይ ለበለጠ መረጃ የፋርም ሬዲዮ ኢንተርናሽናል በሃሰተኛ ዜና ዙሪያ ለስርጭት ባለሙያዎች የተዘጋጀውን መመሪያ ማንበብ ይችላሉ፦ https://training.farmradio.fm/am/fakenewsamharic/

ምስጋና

አዘጋጆች፦ ፓትሪክ ምፓካ - የኔትወርክ ኦፊሰር፣ ማላዊ፣ ማዉሊክፕሊሚ አፎግኖን - የአውታረ መረብ ኦፊሰር፣ ቶጎ፣ ሲልቪ ሃሪሰን - ሥራ አስኪያጅ፣ ሬዲዮ ክራፍት፣ እና ካትሪን በርንሃም, የሬዲዮ አውታረ መረብ አገልግሎቶች አስተዳዳሪ ስራ አስኪያጅ።

ይህ ግብዓት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሃገራት ስኬል ውስጥ ያለው የህይወት አድን የህዝብ ጤና እና የክትባት መረጃ ስርጭት አካል ሲሆን በካናዳ አለም አቀፍ ጉዳዮች በካናዳ መንግስት በኩል የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት ነው።