የተሻሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ

እንደ ስርጭት ባለሙያዎች እና አዘጋጆ፤ በየቀኑ በርካታ ጥያቄዎችን ማንሳታችን አይቀሬ ነው። የምናነሳቸው ጥያቄዎች ስክሪፕቶቻችንን፣ ፕሮግራሞቻችንን እና ሪፖርቶቻችንን ለማዘጋጀት የሚረዱ መረጃዎችን የምናገኝባቸው መንገዶች ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህን ጥያቄዎች የምናነሳቸው በቃለ መጠይቅ መልክ ነው (ውጤታማ ቃለመጠይቅ እንዴት መቅረጽ እና መተግበር እንደሚቻል ለማወቅ እዚህ ይጫኑ)። አብዛኛውን ጊዜ የፈለግነውን መረጃ ለማግኘት ካለን ጉጉት የተነሳ ወይም ተጠያቂው ሊነግረን ይችላል ብለን በምንይዘው ቅድመ-እሳቤ የተነሳ “መሪ ጥያቄዎችን” እንጠይቃለን። የዚህ አይነት ጥያቄዎች ደግሞ ቃለ መጠይቅ እየተደረገ ያለው ሰው በተለየ መንገድ እንዲመልስ በተዘዋዋሪ ስለሚጠይቁ በግልፅ እና በታማኝነት መልስ ለመስጠት አስቸጋሪ የሚያደርጉ ናቸው። ለቃለ-መጠይቅ ሰጪዎች እና አድማጮችዎ ክብር ሲባል፣ እንደጠያቂ እርስዎ ሊሰሙት የፈለጉትን ምላሽ በመገመት መልስ እንዳይሰጡ መሪ ጥያቄ ያልሆኑ፤ የተሻሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ አስፈላጊ ነው።

የተሻሉ ጥያቄዎች” ስንል ምን ማለታችን ነው?

የተሻሉ ጥያቄዎች ገለልተኛ፣ የማያዳሉ እና የተብራራ መልስ ለመስጠት የሚያመቹ ናቸው። ቃለ-መጠይቅ ተጠያቂው ተጽዕኖ ሳይደርግባቸው በራሳቸው አገላለጽ ግልጽ መረጃ በመስጠት ተሞክሮዋቸውን እንዲያጋሩ ይረዷቸዋል።
የተሻሉ ጥያቄዎች መሪ ጥያቄዎችን ይተካሉ። መሪ ጥያቄዎች ለቃለ መጠይቅ ሰጪው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚጠበቅባቸው አቅጣጫ ይሰጣሉ። ቃለ-መጠይቅ ሰጪውን ቃለ-መጠይቅ አድራጊው እንዲሰማው ወደ ሚፈልገው ወይም ወደ ሚጠብቀው መልስ "ይመሩታል"።
የተሻሉ ጥያቄዎች የተሻሉ መልሶችን ያስገኛሉ - ግልጽ፣ ሃቀኛና ገራሚ ምላሾችን ያስገኛሉ

የተሻሉ ጥያቄዎችን መጠየቁ አድማጮቼን በይበልጥ እንዳገለግል በምን መልኩ ይረዳኛል?

  • የተሻሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ ቃለ-መጠይቅ ተደራጊዎች የሚሰጧቸው ምላሾች ለአድማጮችም ጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋሉ - በበቂ ሁኔታ ዝርዝር እና ከርዕሱ ጋር በቀጥታ የተያያዙ ምላሾችን ያስገኛሉ።
  • ቃለ-መጠይቅ የሚደረግላቸው ሰዎች ምላሽ ከመስጠት ሊቆጠቡ ከሚፈልጓቸው ርዕሰ ጉዳዮች የመሸሽ እድላቸውን ይቀንሳል።
  • አድማጮች አንድ ቃለ መጠይቅ የተደረገለት ሰው የሚያምንበትን እና የሚሰማውን በተሻለ ሁኔታ እንዲረዱ ያግዛል።
  • በቃለ መጠይቅ ውስጥ ያልተጠበቀ ይዘትን ከማካተት ረገድ አስተዋጾ ይኖረዋል። መሪ ጥያቄዎች ግን ውስን ምላሽ ብቻ እንዲኖር ያደርጋሉ።
  • ተከታይ ጥያቄዎችን በማንሳት ዝርዝር መረጃ ያላቸውን ምላሾች ለማስገኘት ይረዳሉ።
  • ሐቀኛ ስለሆነ የጋዜጠኝነት ሞያ የሚጠበቅበትን ያሟላል።

የተሻሉ ጥያቄዎችን መጠየቁ የተሻሉ ፕሮግራሞችን ለማዘጋጀት በምን መልኩ ይረዳኛል?

  • የተሻሉ ጥያቄዎችን የመጠየቅ ዲሲፕሊን መማሩ የጥሩ ጋዜጠኝነት መሰረት የሆነውን የማወቅ ጉጉት፣ በመደገፍ የእያንዳንዱ ቃለ መጠይቅ አንቀሳቃሽ ኃይል እንዲሆን ያስችላል።
  • በፕሮግራሙ ውስጥ አድልዎ እንዳይታይ ይከላከላል።
  • ጋዜጠኛው ስለ ታሪኩ ምንነት የሚገምትበት ሳይሆን ታሪኩ ምን አንደሆነ እንዲገነዘብ ይረዳዋል።

እንዴት መጀመር እችላለሁ?

  1. ቃለ መጠይቅዎን ያቅዱ።
  2. የተለያዩ የጥያቄ ዓይነቶችን እና ዓላማዎቻቸውን ይወቁ።
  3. ጥያቄዎችዎትን ሲጽፉ የመሪ ጥያቄ ይዘት ያላቸውን ጥያቄዎች ከማካተት ይቆጠቡ።
  4. ባደረጉት ጥናት ላይ የተመረኮዙ ጥያቄዎችን ያዘጋጁ።
  5. የተለያዩ አይነት ጥያቄዎችን ያዘጋጁ።
  6. ጥሩ ተከታይ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ዝግጁ ይሁኑ

ዝርዝሮች

1. ቃለ መጠይቅዎን ያቅዱ።

ቃለመጠይቆችዎን ማቀዱ ሁል ጊዜ አስፈላጊ ነው። በመጀመሪያ እርስዎ እየፈለጉት ያለውን ልምድ ሊያካፍል የሚችለውን ትክክለኛውን ሰው ማግኘት አለብዎት። ያ ሰው አስፈላጊው እውቀትና ልምድ አለው ማለት ነው። ተገቢውን ሰው ከመረጡ በኋላ ከእነሱ ምን መማር እንደሚፈልጉ ይወስኑ። በትክክል ማወቅ የሚፈልጉትን ማወቁ የተሻሉ ጥያቄዎችን ለመንደፍ ጠቃሚ ነው።

በርዕሱ ላይ በቂ ጥናት ማድረጉም አስፈላጊ ነው። ስለ ርዕሰ ሃሳቡ እና ቀለ መጠይቅ ሰጪው በቂ መረጃ መኖሩ የተሻለ ጥያቄዎችን እንዲጠይቁ ያግዝዎታል።

ኒማ፣ ባለቤቷ ጎድፍሬይ እና ሁለት ልጆቻቸው አነስተኛ ገብርና ላይ የተሰማሩ ናቸው። የሚኖሩት በታንዛኒያ ዶዶማ ደረቅ አካባቢ በሚገኝ አንድ ሄክታር ተኩል መሬት ላይ ነው። በቆሎ፣ የተወሰነ ካሳቫ እና ስኳር ድንች ያመርታሉ። የኒማ ቤተሰብ ከምርቶቻቸው ራሳቸውን ከመመገብ አልፎ ትንሽ ገንዘብ ማግኘት ችለዋል። ሆኖም ከሚያመርቱት እብዛኛው እየባከነባቸው እንደሆነ የኤክስቴንሽን ኦፊሰር ነግሯቸዋል። በየአመቱ 20 በመቶ የሚሆነው የበቆሎ እህል ምርት በመከር ወቅት ሲሰበሰብ እና ተገቢ ባልሆነ ማከማቻ ስለሚቀመጥ እንደሚወድም ለኒማ ነግሯታል። በነፍሳት አማካኝነት እህሉ ላይ የሚደርሰው ጉዳት የገንዘብ ብክነትንም ያስከትላል። ከአጎራባች አርሶ አደሮች ጋር፣ ኒማ እና ጎድፍሬ ስለተሻለ የመከር ወቅት እህል አሰባሰብ እና ተገቢ የእህል ማከማቻዎችን በሚመለከት የበለጠ እንዲማሩ መክሯቸዋል። ኒማ ይህን ማድረግ ብትፈልግም ባለቤቷ ግን ከአዳዲስ ዘዴዎችን ይጠራጠራል፤ እንደ ጎረቤቶቻቸው ማረስን ይመርጣል። ጎልቶ መውጣት ወይም መሳለቂያ መሆን ያሳስበዋል።

በዚህ ሁኔታ ከኒማ ጋር የሚደረግ ቃለ ምልልስ አሁን ያላትን የሰብል መሰብሰብ እና የማጠራቀሚያ ዘዴዎችን የሚዳስስ እንዲሁም እሷ እና ባለቤቷ እንደሌሎች በክልሏ ውስጥ እንደሚታየው አዳዲስ ዘዴዎችን ለመሞከር የማይፈልግበትን ምክንያት ለማወቅ የሚጥር ይሆናል። በኒማ ቤተሰብ ውስጥ ባሏ አብዛኛውን ጊዜ ውሳኔዎች የሚያስተላልፍ ስለሆነ ይህ ጉዳይ በጥንቃቄ ሊታይ ይገባል። እርሻን የሚያከናውንበትን መንገድ እንዲቀይሩ ለማሳመን መጣር ውሳኔ የሚያስተላልፍበትን መንገድ ለማስለወጥ መጣር ማለት ነው። በእንደዚህ አይነት ሁኔታ መረዳት የሚገባን ኒማ ጥያቄዎቹ ከእርሻ ስራ አልፈው ሌሎች ርዕሶችንም መዳሰሳቸው እንደማይቀር መረዳቷን፣ ግብርናን በሚመለከት ውሳኔዎች እንዴት እንደሚወስኑ መጠይቁ ሊዳስስ እንደሚችል በተጨማሪም ኒማ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኗን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው። የቃለ መጠይቅ እቅዱ የሚሆነው እሷን በእርሻዋ ሄዳ መጎብኘት እና ቃለ ምልልሱን በቅርብ ጊዜ ከተሰበሰበው የበቆሎ እህል ከረጢት አጠገብ ቆማ ማድረግ ነው። ቃለ መጠይቁ የሚጀምረው የቆመችበትን ቦታ፣ የዘንድሮው ሰብል ምን ያህል የተሳካ እንደነበር፣ እሷ እና ጎድፍሬይ በቆሎውን እንዴት እንደሰበሰቡ፣ እንዴት እንደሚያከማቹ እና ኪሳራን ለመቀነስ የሚጠቀሟቸውን ዘዴዎች ለመቀየር ያስቡ እንደሆነ በመግለጽ ይጀምራል። በዚህ ጊዜ ስለቤተሰብ ሁኔታ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል። የኤክስቴንሽን ኦፊሰሩን በማነጋገር እነዚህ ሁለቱ አርሶ አደሮች በበቆሎ አሰባሰብ፣ በማከማቻ እና በማጓጓዝ ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው የበቆሎ እህል ሊያጡ እንደሚችሉ እና በዚህም ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንደሚያጡ ተገንዝበዋል።

2. የተለያዩ አይነት ጥያቄዎችን እና አላማቸውን ይወቁ።

የተሻሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ ላይ እንቅፋት ከሚሆኑት ነገሮች መሃል ትልቁ መሪ ጥያቄ ነው።
ተጠያቂውን ወደሚፈልጉት ምላሽ እየመሩ ስለሆነ መሪ ጥያቄዎች በፍጥነት ወደ ነጥብዎ ያደርስዎታል። ይህ ግን እንደ ችግር የሚታየው የእርስዎ ነጥብ እንጂ የተጠያቂው አለመሆኑ ነው።

የመሪ ጥያቄ ትርጉም፦ መሪ ጥያቄ አንድን የተለየ ምላሽ የሚያበረታታ ጥያቄ ነው፣ አብዛኛውን ጊዜ በቃለ-መጠይቅ አድራጊው የሚፈለግ ወይም የሚጠበቅ ምላሽን የሚያስገኝ ነው። መሪ ጥያቄዎች ተጠያቂውን ያሚመሩበት ምክንያት በጥያቄው አደረጃጀት ነው። አንዳንድ ጊዜ መሪ ጥያቄዎች የሚፈለገውን መላሽ በራሳቸው ሀረግ ሊያካትቱ ይችላሉ። ለምሳሌ፤
ኒማ የበቆሎ ምርትሽን እንደሰበሰብሽ አያለሁ ግን ምርታማ አመት እንዳልነበረ ያስታውቃል። በቂ ዝናብ አልነበረም?
እውነታው ግን ኒማ ጥሩ የሚባል ምርታማ አመት እንደነበራት ነው። በቆሎን ለማምረት ያላት ቦታ ግን ውስን ነው። ጥያቄው ግን ይህንን እንድታስረዳ ስለማይጋብዝ አስቸጋሪ ይሆንባታል። ቃለ-መጠይቅ አድራጊው ከመነሻው አቋሙን የሚገልጽ አስተያየት ይዞ ስለተነሳ ኒማ ይህንን መቃወሙ ጨዋነት የጎደለው እንደሆነ አድርጋ ልትቆጥረው ትችላለች። ጥያቄው በቀጥታ ስለ ሰብሉ ሳይሆን ስለ ዝናብ ሁኔታው ነበር። በዚህ ሁኔታ የተሻለው ጥያቄ የሚሆነው፦

የዘንድሮ የበቆሎ ምርት እንዴት ነበር?

ኒማ ይህን ጥያቄ በቀላሉ ልትመልሰው የምትችለው ነው። የበቆሎ ሰብል ምርቷ ከአማካይ በላይ ነበር። ቃለ ምልልሱ እየተከናወነ ያለው በከረጢት ሰብስባ ካስቀመጠችው የበቆሎ ምርቷ አጠገብ ስለሆነ ወደ እህሉ እየጠቆመች ማስረዳት ትችላለች። የድምጽ ገለጻዎች ምስልን የመሳል ጥንካሬ ስላላቸው አድማጮችም በአይነ ህሊናቸው እንዲስሉት ይረዳቸዋል።.

መኸሩን በሚመለከት ጥሩ ተከታይ ጥያቄ የሚሆነው፦

ምርቱ ላይ ምን ተጽዕኖዎች ነበሩ?

ከቃለ መጠይቅ አድራጊው በተሻለ ምን ያህል ዝናብ ዘንቦ እንደነበር እንዲሁም ሌሎች ተጽዕኖዎች የነበሩ እንደሆነ ኒማ ታውቃለች። በአየር ሁኔታ ላይ ማተኮር እንዳለባት ሳይሰማት ስለ ራሷ ልምድ ብዙ ማውራት ትችላለች። የ“ምን ምክንያቶች…?” ብሎ የሚነሳው ጥያቄ ተፈጥሮው ኒማ ስላጋጠሟት ጉዳዮች በነጻነት እንድትናገር ይረዳታል። ተከታይ ጥያቄዎችም በእሷ ምላሽ ላይ የተመሰረቱ ይሆናሉ።

መሪ ጥያቄዎችን የሚረዱበት ሌላው መንገድ ቅድመ ግምታዊ ጥያቄዎች፣ መርማሪ ጥያቄዎች እንዲሁም መልስ አዘል ጥያቄዎች በመሆናቸው ነው።

ቅድመ- ግምታዊ ጥያቄዎች፦ እነዚህ ጥያቄዎች በቃለ-መጠይቅ ተደራጊው ተፈላጊ ምላሽ የሚያሰጡ ሆነው የሚታዩ እንዲሁም የበለጠ ቃለ መጠይቅ ተደራጊውን ተጠያቂ የሚያደርጉ ወይም የተለየ ምላሽ እንዲሰጡ የሚያደርጓቸው ናቸው።

ኒማ የበቆሎ ምርጥ ዘር ትጠቀሚያለሽ?

ጥያቄው ገለልተኛ ይመስላል እና መጀመሪያ ላይ አይመራም። ነገር ግን የተሻሻሉ ዝርያዎችን መጠቀም ጥሩ ነገር እንደሆነ ወይም የቃለ መጠይቅ አድራጊው ፕሮጀክት እየሞከረ ያለው ነገር ስለሆነ ኒማ አዎ እንድትል አስቀድሞ ሊገፋፋት ይችላል። በአጠቃላይ ምላሽ ሰጪዎች ቃለ-መጠይቅ አድራጊውን የሚያስደስቱ መልሶች እና እራሳቸውን በጥሩ ሁኔታ የሚያሳዩ ምላሾችን የመስጠት አዝማሚያ እንደሚታባቸው ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። ሊጠየቅ የሚገባው የተሻለው ጥያቄ፡-

የሚትጠቀሚያቸው ዘሮች ምን ዓይነት ናቸው ኒማ?

ስለዚህ፣ ቅድመ ሁኔታ ጥያቄዎችን ከመጠየቅ ለመቆጠብ፤ ሀ)በማህበረሰቡ ተደጋፊ ናቸው ተብለው የሚቆጠሩ ምላሾችን የሚጠቁሙ ቃላት መቆጠብ፣ እና ለ)በተቻለ መጠን አጠቃላይ ጥያቄ ሆነው ግን የሚፈልጉትን መረጃ የሚያደርስዎት ጥያቄዎችን ይጠይቁ።

ቀጣዮቹ ሌላ የቅድመ- ግምታዊ ጥያቄ ምሳሌ እና አማራጭ የተሻለ ጥያቄ ናቸው።

በዚህ አካባቢ ያሉ አንዳንድ አርሶ አደሮች የሚያጋጥማቸው የሰብል ብክነት አንቺንም እንዳያጋጥምሽ አዲሱን እና ውጤታማ የሆነውን የሰብል መሰብሰቢያ ዘዴዎችን መጠቀም ትመርጫለሽ?

“ትመርጫለሽ” እና “ውጤታማ” የሚሉት ቃላቶች ኒማ ዘዴዎቹን ብትወድም ባትወድም በማህበረሰቡ ዘንድ ተመራጭ የሆነውን ምላሽ ያመለክታሉ። ያንን ጥያቄ ስትመልስ የበለጠ በሐቀኝነት እንድትመልስ በሚያስችላት በእነዚህ ገለልተኛ ጥያቄዎች ይተኩ።

ቅድመ ወይም ድህረ-ምርት ወቅት የሰብል ብክነት አጋጥሞሽ እንደሆነ ለይተሽ ታውቂያለሽ?

ለዚህ ምክንያቱ ምን ይመስልሻል?

አንዳንድ አርሶ አደሮች ለመተግበር እየጣሩ ስላሉት የተለያዩ የሰብል አሰባበብ ዘዴዎች ምን ይሰማሻል?

መሪ ጥያቄዎችን ከመጠየቅ በመቆጠብ፣ ኒማ በህይወት ልምዷ ላይ ተመርኩዛ ልትመልሳቸው የምትችላቸውን ተጨማሪ ጥያቄዎችን መጠየቅ ይችላሉ። እዚህ ባለሙያዋ እሷ እንጂ ጠያቂው አይደለም። ገዳቢ ያልሆኑ ጥያቄዎች እውቀቷን እንድታካፍል እድል ይሰጧታል።

በመጀመሪያው ጥያቄ ውስጥ "ለይተሽ" የሚለውን ቃል አጠቃቀም ሳቢ ምርጫ ነው። ጥናት አድራጊዎች እንደሚገልጹት “ለይተሽ ታውቂያለሽ…” የሚሉትን ቃላት መጠቀሙ ኒማ አዎንታዊ መልስ እንድትሰጥ እንደማይጠበቅባት ይጠቁማሉ። “መከሰት” የሚለውን ቃል አለመጠቀም ያንን ተስፋ ያስወግዳል፣ ኒማ ከልምዷ ለመናገር ነፃ ትቷታል። ጥያቄው ውስጥ “ለይተሽ” የሚለውን ቃል አለመጠቀሙ የሚጠበቅባትን ምላሽ ወደጎን በመተው ኒማ በነጻነት ልምዷን እንድታካፍል ይረዳታል።

መሪ መመርመሪያዎች ፦ መመርመሪያዎች የተጠያቂውን መልስ ወይም መግለጫ በጥልቀት ለመመልከት ያገለግላሉ። በቃለ መጠይቅ ውስጥ በጣም ጠቃሚ እና ተገቢ ቢሆኑም መሪ ምርመራዎች ግን ጠቃሚ አይደሉም። ቃለ መጠይቅ ተደራጊውን በዘዴ (ወይንም በዘዴ ባይሆንም) በተወሰነ መንገድ ምላሹን እንዲመልስ ይመራሉ፣ በመሰረቱ “ቃላቶችን በቃለ መጠይቅ ተደራጊው አፍ ውስጥ ማስገባት” እንደማለት ነው።

“በኤክስቴንሽን ኦፊሰሩ የቀረቡት አዲስ የማከማቻ አማራጮች አይጠቅሙም እያልሽ ነው?”

ኒማ ለቃለ-መጠይቅ አድራጊው እንደተናገረችው ሁልጊዜም እንደምታደርገው በቆሎዋን በከረጢት ውስጥ ማከማቸቱ ለእሷ እና ለጎድፍሬይ ተስማምቷቸዋል። ቃለ-መጠይቁን ያደረገው ደግሞ እዚህ እንደተመለከትነው ምን ለማለት እንደፈለገች እንድታብራራ መሪ መርማሪ ጥያቄ አስከትሎ ጠየቃት። መርማሪው ጥያቄ በመጀመሪያ በተጠያቂዋ አእምሮ ውስጥ ላይኖር የሚችልን ሀሳብ ይጠቁማል። በተጨማሪም ኒማ አመቺ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ እንድትሆን ያረጋታል ምክንያቱም እሷ ከኤክስቴንሽን ባለሙያው በበለጠ እኔ ብልህ ነኝ ያለች ያስመስላታል።

ከዛ ይልቅ መመርመሪያ ጥያቄው ክፍት ሊሆን ወይም ገዳቢ ያልሆነ ሊሆን ይገባል፤ ለምሳሌ፤

ይህን ስትይ ምን ማለትሽ ነው? ወይም - እባክሽን የበለጠ ማስረዳት ትችያለሽ?

መልስ አዘል ጥያቄዎች፦ መልስ አዘል ጥያቄ የሚያመለክተው እውነት ባይሆንም አንዳንድ እውነታዎች በውስጡ መያዙን ነው። የዚህ አይነት ጥያቄ ምላሽ ሰጪውን አጣብቂኝ ውስጥ ይከታል። ይህ ቀጣዩ ኒማ የተጠየቀችውን ጥያቄ እንደ ምሳሌ እንውሰደው፦

የኤክስቴንሽን ኦፊሰሩ 20% ምርትሽን እያጣሽ እንደሆነ ሲነግርሽ ውሸቱን መስሎሽ ነበር?

“ውሸቱን” የሚለው ቃል በጣም ጠንካራ ቃል ነው። በዕርግጥም የኤክስቴንሽን ኦፊሰሩ ውሸታም መሆኑን በተዘዋዋሪ በመጥቀስ ጥያቄውን ምላሽ አዘል ያደርገዋል። ኒማ ስለ ሰውዬው ምክንያት ምንም ስለማታውቅ እሷን ይህን ጥያቄ መጠየቁ ተገቢ አይደለም። እውነት ወዳልሆነ ወይም ወደተዛባ መልስ ሊመራ ይችላል። ለኤክስቴንሽን ኦፊሰሩም ተገቢ አይደለም።

ይህንኑ ጥያቄ በቀጣዩ የተሻለ መንገድ መጠየቅ ይቻላል፦

የቆሎ መርትሽን ገበያ ላይ ከማድረስሽ በፊት 20% እንደሚባክን የኤክስቴንሽን ኦፊሰሩ የገለጸውን እንዴት ትመለከችዋለሽ?

በተሞክሮዋ ላይ በመመስረት ኒማ ይህ ጥሩ ግምት መሆኑን ልትናገር ትችላለች። የሚፈለገው የእሷ ታሪክ፣ የእሷ ተሞክሮ ነው።

3. ከመሪ ጥያቄዎች በመቆጠብ ጥያቄዎችዎን ይጻፉ።

መሪ ያልሆኑ ጥያቄዎች የቃለ-መጠይቅ አድራጊውን አድልዎ ወይም የሚጠብቃቸውን የሚያስወግዱ ክፍት ወይም ገዳቢ ያልሆኑ ጥያቄዎች ናቸው። ቃለ-መጠይቆችን በመረጡት መንገድ የመመለስ ነፃነትን ለመፍቀድ የተነደፉ ናቸው። በጣም ውጤታማ የሆኑት መሪ ያልሆኑ ጥያቄዎች ብዙውን ጊዜ ጠያቂው ፈጽሞ ያላሰበውን ግንዛቤዎችን እና ሀሳቦችን ወደሚያሳዩ ውይይቶች ይመራሉ። መሪ ባልሆኑ ጥያቄዎች፣ ተጠያቂ ከጠያቂው ጋር ለመስማማት ወይም ለመቃወም አይገደድም፣ ወይም ተጠያቂው በጠያቂው አስተያየት ተጽዕኖ አይደረግበትም።

ቃለ መጠይቅ አድራጊው ለኒማ ሊያቀርባቸው የሚገቡ ክፍት ወይም ገደብ የሌላቸው ጥያቄዎች ምሳሌዎች የሚከተሉት ናቸው።

እርሻሽ ምን እንደሚመስል መግለጽ ትችያለሽ?
በዚህ አመት የበቆሎ ምርትሽ እንዴት ነበር?
በምርቱ ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩ ነገሮች ምን ነበሩ?
ምን አይነት ዘር ነው የምትጠቀሚው ኒማ?
ዘሮቹ ከውጤታማነት አንጻር እንዴት ነበሩ?
አንቺ እና ጎድፍሬይ በቆሎ እንዴት ዘርታችሁ ምርቱን እንደምትሰበስቡ አስረጂኝ።
አንቺ እና ጎድፍሬይ እርሻውን በሚመለከት ውሳኔ እንዴት ነው የምትወስኑት?
በጋራ መስራቱ ለአንቺ አስፈላጊ ነው?
በመኸር ወቅት የተወሰነ የሰብል ብክነት ደርሶባችሁ መሆን አለመሆኑን የምታውቂው ነገር አለ?
ለዚህ ምክንያቶቹ ምን ይመስሉሻል?
አንዳንድ አርሶ አደሮች በሙከራ መልክ እየተገበሩት ስላሉት የተለያዩ የአዝመራ ዘዴዎች ምን ይሰማሻል?
በቆሎ ሰብሉን በከረጢቶች ውስጥ ለማስቀመጥ ለምን መረጥሽ?
በዚያ መንገድ ማስቀመጡን እንዴት ተማርሽው?
ሌላ ስለ ምን የማከማቻ ዘዴዎች ሰምተሻል?
አንቺ እንደተረዳሽው የእያንዳንዱ ዘዴ ጥቅም እና ችግሮች ምንድን ናቸው?
ለወደፊቱ መኸር እና እህል አከመቻቸት ዙሪያ ላይ ምን አቅደሻል?

እነዚህ ሁሉ ክፍት ወይም ገዳቢ ያልሆኑ ጥሩ ጥያቄዎች ናቸው። ነገር ግን የተሻሉ ጥያቄዎች በሚዘጋጁበት ጊዜ ከግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ሌሎች ነጥቦችም አሉ።

4. በጥናትዎ ላይ በመመስረት ጥያቄዎችን ያዘጋጁ።

ከመጠን በላይ አጠቃላይ ሃሳቦች ላይ አያተኩሩ። በተቻለ መጠን ቀጥተኛ ጥያቄዎችን ያንሱ። ለምሳሌ እንደ ተከታዩ አይነት ያለ ጥያቄ አይጠይቁ፤

"በበቆሎ ምርት ተባዮችን ለመቋቋም ምርጡ መንገድ ምንድነው?"

የበቆሎ ተክሎችን እና የተከማቸ በቆሎን የሚያበላሹ ብዙ አይነት ተባዮች አሉ። ስለዚህ ለጥያቄው እውነተኛ መላሽ ሊሆን የሚችለው “እንደ ሁኔታው ነው”የሚለው ይሆናል። ስለዚህ ጥያቄዎ ቀጥተኛ መሆኑን ያረጋግጡ። ለምሳሌ፡-

"ከተዘራ ከስድስት ሳምንታት በኋላ ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምችን ለመቋቋም ምርጡ መንገድ ምንድነው?"
"በተሰበሰበው የበቆሎ እህል ውስጥ ነቀዝ እንዳያጠቃው ምን ያደርጋሉ?"

በጥያቄ ውስጥ “የሚመከር” ወይም “ትክክለኛ” የሚሉትን ቃላት በጭራሽ አይጠቀሙ። ለምሳሌ፦

“በቆሎን ለማከማቸት የሚመከረውን የብረት ሴሎ ይጠቀማሉ?”

ጥያቄዎን በዚህ መንገድ የመግለጽ ችግሩ አንዳንድ የተመከረውን የእህል ማከማቻ አማራጭ የማይጠቀሙ ሰዎች እራሳቸውን በመጥፎ እንዳይታይባቸው ሲሉ ብቻ የማከማቻ ዘዴውን እንደሚጠቀሙ ወይም ሊጠቀሙ እንዳቀዱ ሊነግሩዎት ይችላሉ። እንዲሁም ኒማ የተመከረውን እየሰራች እንደሆነ ታምን ይሆናል ነገር ግን የተመከረውን ሂደት ሙሉ በሙሉ አልተረዳችም ይሆናል። ጠያቂው መረጃን ከመገመት መቆጠብ አለበት። ክፍት ወይም ገዳቢ ያልሆኑ ጥያቄዎች ግምቶችን ከመውሰድ ይታደጋሉ።

ጥናት በሚያደርጉበት ወቅት አንድን ችግር በምን በምን በተለያዩ መልኩ ማየት እንደሚቻል ይረዳሉ። ለምሳሌ የተባይ ችግርን ወይም የአፈር ለምነት ላይ ያለ ችግርን ወይም ሰብል መሰብሰብ ላይ ያሉ ችግሮችን። ቀጥተኛ ምሳሌዎችን መስጠቱ ቀጥተኛ ምላሾችን እንዲያገኙ ይረዳዎታል።

“በአካባቢያችሁ ያሉ አርሶ አደሮች በጋራ አዋጥተው አንድ ሜካኒካል ማጨጃ ቢገዙና በየተራ ቢጠቀሙት ስለሚለው ሃሳብ ምን ይመስልዎታል?”

እንደ ጠያቂ ማወቅ የሚፈልጉትን ነገር ለይቶ መረዳቱ እንደ ኒማ ላሉ ተጠያቂዎች በቀጥታ የሚያውቁት ነገር ላይ ተመርኩዘው የተሻለ ምላሽ እንዲሰጡ ይረዳቸዋል። እንዲሁም ለአድማጮችዎም የተሻሉና የበለጠ ዝርዝር መረጃዎችን ይሰጣል።

5. የተለያዩ አይነት ጥያቄዎችን ያዘጋጁ

ማንኛውም ቃለ መጠይቅ የሚከተሉት የተቀላቀሉበት ሊሆን ይገባል 1) መረጃን የሚያስገኙ ጥያቄዎች እና፣ 2) የጠያቂውን ባህሪ ወይም ስብዕና እና ስሜት የሚያጎሉ ጥያቄዎች። (ያስተውሉ፣ ሁለቱንም አይነት ጥያቄዎች መጠየቅ አስፈላጊ ቢሆንም፣ በተግባር ግን፣ ግለሰባዊ ጥያቄዎች ብዙ ጊዜ መረጃን እና ባህሪን/ስብዕናን/ስሜትን ይፈጥራሉ።)

እስካሁን፣ አብዛኛዎቹ ለአብነት የተዘረዘሩት ጥያቄዎቻችን እውነታን ለመፈለግ የሚነሱ ናቸው። ኒማን ስለ ሰብል፣ የመኸር ዘዴ እና የማከማቻ አማራጮችን ጠየቅናት። ግን እንደ ሰው፣ እንደ ሚስት፣ እንደ እናት እና እንደ ሥራ ፈጣሪ ማን እንደሆነች ብዙም አናውቅም። ስለ ተስፋ እና ህልሞቿ፣ ስጋቶቿ አናውቅም።

ከዚህ በኋላ እርግጠኛ ለመሆን፣ ለፕሮግራማችን ብዙ ላያስፈልገን ይችላል። ነገር ግን የረዥም ጊዜ የስርጭት ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች አድማጮች ስሜታቸውን ሊጋሩት የሚችሉ ሰዎችን በትኩረት እንደሚያዳምጡ ይነግሩናል። ጎረቤቶች እና ጓደኞች ይሆናሉ፤ ብዙውን ጊዜ አርአያ ይሆናሉ፤ እርሻን በሚመለከት ይጋራሉ። እነዚህ አርአያ የሆኑ ሰዎች የመጡበትን ማህበረሰብ ማንፀባረቅ ይኖርባቸዋል።

ከላይ ያሉት ጥያቄዎች ዓይነት የምትጠይቋቸው ጥያቄዎች ቃለ መጠይቅ ተደራጊዋ ታሪኳን እንድትናገር ይረዳታል። አድማጮች ከመጠይቁ ከሚረዱት በተጨማሪ የሷን ስሜት እና ግላዊ ሁኔታ እንዲረዱ ከማድረግ በላይ (የምትኖርበት፣ የቤተሰቧ አባላት ማንነት፣ የእርሻ መሬቷ ስፋት፣ ምን ዓይነት ሰብል ታመርታለች፣ ምኞቷ እና ሕልሟ) የቶቹን መሰናክሎች ወይም ችግሮች አሸንፋ ማለፍ እንደነበረባት እንድትገልጽ ማድረግ ይኖርቦታል። እነዚህ ተሞክሮዎችዋ በአብዛኛዎቹ አድማጮችዎ ዘንድ የተለመዱ ሆነው ይገኛሉ።

የሚከተለው ስለ ቀሪው የቃለ-መጠይቁ አወቃቀር እና ስለሚጠይስቁት ጥያቄዎች ዓይነት የሚያስረዳ መንገድ ነው። የትረካ ቅስት ተብሎ የሚገለጽ ሲሆን እስከ መጨረሻው ጫፍ ድረስ እየገነባ የሚደርስ ነው። መጨረሻው ጫፍ ተደረሰ የሚባለው ቃለ መጠይቅ ተደራጊዋ የነበረውን ችግር እንዴት እንደተፈታ ስትገልጽ ነው። ጥያቄዎችዎ ክፍት መሆናቸውን ወይም ገዳቢ አለመሆናቸውን ያረጋግጡ፣ ዝርዝር ገለጻዎችን ያበረታቱ፣ ቃለ መጠይቅ ተደራጊዋ ታሪኳን በምክንያታዊ ቅደም ተከተል እንድትናገር ይርዷት።

ቀጣዮቹ በጥያቄዎችዎ ትኩረት ሊሰጧቸው የሚገቡ ናቸው።

  • ችግሩን ለመፍታት ምን ዓይነት ልምዶችን እንደሞከሩ፣
  • አንዳንድ ነገሮች ወይም ልማዶች እንዴት እና ለምን እንዳልተሳኩ፣
  • ምን ዓይነት ስጋቶች ነበሩ፣
  • ምን አማራጮች እንደነበራቸው፣
  • የትኞቹን አማራጮች እንደመረጡ እና ለምን አነዛን አማራጮች እንደመረጡ፣
  • በምን ሰዓት ላይ ለችግራቸው መፍትሄ እንዳገኙ እንደተሰማቸው፣
  • ማን እንደረዳቸው፣ እና
  • የራሳቸው፣ የቤተሰባቸው እንዲሁም የማህበረሰቡ ሁኔታ እንዴት እንደተለወጠ።

ታሪኩ ሲገለጥ፣ ስላለው ሁኔታ ተጠያቂ ምን እየተሰማቸው መሆኑን አድማጮች መረዳታቸው ይጠቅማል። ይህንኑ የሚገልጹ ጥያቄዎችን ይጠይቁ። በተለምዶ፣ እንደዚህ አይነት ጥያቄዎች የሚጀምሩት “ስለ . . . እርስዎ ምን ይሰማዎታል…” ግን ሌሎች መንገዶችም አሉ። እንደሚከተሉት ያሉ መሪ ስሜታዊ ጥያቄዎችን ከመጠየቅ ግን ይቆጠቡ።

. . . ሲሆን ሳይናደዱ አልቀሩም
ወይም

. . . ሲሆን ምን ያህል ደስተኛ ነበሩ?

በተጨማሪም አንዳንድ ተጠያቂዎች ስለራሳቸው እና ስሜታቸው ለመናገር ያላቸው ተነሳሽነት እምብዛም ይሆናል። ስሜትን የሚሹ ጥያቄዎችን ከመጠየቅዎ በፊት ከተጠያቂ ጋር መተማመንን መፍጠር ይኖርብዎታል።

ከስር ያሉ ኒማ ባህሪዋን እና ስሜቷን እንድታሳይ የሚሹ አንዳንድ ጥያቄዎች ነቸው።

በመጀመሪያ የዘር መዝሪያ ወቅት ምን ተሰማሽ?
በሁሉን አውዳሚ ተምች ምክንያት ምን ያህል የበቆሎ ሰብል እንዳጣችሁ ስትገነዘቡ ለአንቺ እና ለጎድፍሬይ ሁኔታው እንዴት ነበር?
ልጅሽ ለመጀመሪያ ጊዜ በመኸር ወቅት ሲያግዝሽ የነበረውን ሁኔታ መግለፅ ትችያለሽ?
እርሻሽን በሚመለከት ለወደፊቱ ምን ትመኛለሽ?

እነዚህ ጥያቄዎች በርካታ አድማጮችን ሁኔታ ሊዳስሱ የሚችሉ ናቸው፤ ምናልባትም ኒማ የምትሰጠውን ምላሽ አድማጮችም ሊጋሩት የሚችሉት ነው። አሷን ከመተዋወቃቸውም በተጨማሪ ስለእርሻ ልምዷ የምትናገረውን መስማት ይፈልጋሉ።

6. ጥሩ ተከታይ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ዝግጁ ይሁኑ
ክፍት የሆነ ወይም ገዳቢ ያልሆነ ጥያቄ ጥሩ ቢሆንም፣ ብዙ ጊዜ ቃለ መጠይቅ የሚደረጉት እርስዎ የሚፈልጉትን ምላሽ ሁሉ አይሰጥዎትም።

ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ጥያቄው ግልጽ እና ቀጥተኛ በሆነ መጠን መላሹም እኝደዛው ቀጥተኛ እና ግልጽ ይሆናል። አብዛኛውን ጊዜ ግን ሳይገለጹ የሚቀሩ ዝርዝሮች፣ የሚመረመሩ ስሜቶች፣ ተጨማሪ ማብራሪያዎች ይኖራሉ።

ተከታይ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ዝግጁ መሆን አለብዎት። ያ ማለት ደግሞ ተጠያቂ የሚናገሩትን በጥሞና ማዳመጥ ይኖርብዎታልማለት ነው።

በቅድሚያ የጥያቄ ዝርዝር ማዘጋጀቱ ጠቃሚ የሚሆነው እዚህ ላይ ነው።

ቀጣዩ ዋና ጥያቄን አስቀድመው በአእምሮዎ ውስጥ ካኖሩት ስለሱ ሳይጨነቁ ለቀድሞው ጥያቄ በተሰጠው ምላሽ ላይ ሙሉ በሙሉ ማተኮር ይችላሉ - ምላሹ ትርጉም አለው? በቂ ማብራሪያ ተደርጎበታል? ሁሉም ዝርዝሮች ነበሩት? ስሜታዊ ይዘቱ አለ? ምሳሌ፡-

ዋና ጥያቄ፦

የዘንድሮ የበቆሎ ሰብል እንዴት ነበር ኒማ?

መልሷ ላይ በመመርኮዝ ሊጠየቅ የሚችል ተከታይ ጥያቄ፦

ከአምናው ጋር ማወዳደር ትችያለሽ?
ያምናው በምን መልኩ የተሻለ ነበር?
ያን ልታብራሪው ትችያለሽ?
ከዘንድሮው መኸር በኋላ ምን ተሰማሽ?

ተከታይ ጥያቄዎችን መጠየቅ ማዳመጥ ብቻ ሳይሆን ተለዋዋጭነትንም ይጠይቃል። የጥያቄዎች ዝርዝር በማስታወሻ ደብተርዎ ወይም በስልክዎ ላይ አዘጋጅተው ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን ውይይቱ ወደ ያልታቀደ አቅጣጫ ከተዘዋወረ፣ የሚጠይቁት ነገር ሊኖርዎት ይገባል። እቅድ ማውጣት አስፈላጊ ቢሆንም፣ ለሚሰሙት ነገር ምላሽ መስጠትም አስፈላጊ ነው።

አንዳንድ ጊዜ ተከታይ ጥያቄዎች የቃለ መጠይቅ ሰጪውን ምላሽ የሚፈታተኑ መሆን አለባቸው። አንዳንዴ ደግሞ ተከታይ ጥያቄዎች ውስብስብ የሆነን ምላሽ በተሻለ ለመረዳት ሊያግዝዎት ይችላሉ። አንድ ሰው ምን ማለቱ እንደሆነ እርግጠኛ ካልሆኑ፣ “እባክዎ አስረዱኝ” ወይም “አንድ ምሳሌ ሊሰጡኝ ይችላሉ?” ማለቱ ይሻላል። ቃለ መጠይቅ የማድረግ እድሉ በአብዛኛው አንዴ ብቻ የሚያገኙት ነው።

ቀጣዮቹ ሶስት ዘዴዎች ተከታይ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ የሚረዱ ናቸው

ሀ. የመጀመሪያውን ጥያቄዎን ትንሽ ለየት ባለ ሁኔታ እንደገና ይጠይቁ። ተመሳሳይ ጥያቄ ሁለት ጊዜ ለመጠየቅ አይፍሩ። ቃለ መጠይቅ የሚደረገው ሰው መጀመሪያ የተጠየቀውን ጥያቄ በበቂ ሁኔታ ሳይመልስ ወይም ትክክለኛ ምላሽ ካልሰጠ፣ “ይህንኑ ጥያቄ በሌላ መንገድ ልጠይቅዎ…” ማለት ይችላሉ። ይህ ውጤታማ የሚሆነው ተጠያቂው ምላሽ ሳይሰጡ እንዲያልፉ እንደማትፈቅዱላቸው ስለሚያሳውቅ ነገር ግን ቢያንስ ምናልባት የመጀመሪያ ጥያቄ በበቂ ግልፅ እንዳልሆነላቸውም የሚለውን ምክንያት ስለሚሰጣቸው ከእፍረትም ያድናቸዋል።

ጥንቃቄ፡- ጥያቄውን ድግመው ሲጠይቁ የመጀመሪያውን የገለጹበትን መንገድ መቀየርዎን ያረጋግጡ፣ ካልሆነ ግን ተቃዋሚ ጥያቄ ሊመስልብዎት ይችላል። ዋናው ነገር ጥያቄውን በሌላ መንገድ መጠየቅ እና ይህን እያደረጉ መሆኑን ለተጠያቂው ማስታወቁ ነው።

ለ. የተጠያቂውን ምላሾች በንቃት በማዳመጥ እርስ በርስ ያገናኟቸው።

ቃለ መጠይቅ ተደራጊ የሚናገሩትን በደንብ ለመረዳት አንዱ ጥሩ ስልት ምላሻቸውን ቀደም ብለው ከተናገሩት ነገር ጋር ማገናኘት ነው። ይህ አላማው አንድን ሰው ሲዋሽ ለመያዝ መሞከር ሳይሆን በመልሶቹ መካከል ያሉትን ነጥቦች ማገናኘት ነው። “ኦሃ ያኔ እንደነበረው እርስዎ … ማለት ነው?” ወይም፣ “ቀደም ሲል . . . ሲሉ የተናገሩት ይህን ለማለት ነው ማለት ነው?” ተጠያቂውን በደንብ እንዲረዱት ከማድረጉም በላይ በጥሞና እየሰሙ እንደሆነ ይነግራቸዋል በተጨማሪም በነጥቦች መሃል እሱ ወይም እሷ ያላስተዋሉትን ግንኙነት እንዲያስተውሉ እድሉን ይሰጣቸዋል። መረጃን መስማት ብቻ ሳይሆን ለማዋሃድ ይረዳዎታል።

ጥንቃቄ፡- ይህን ከልክ በላይ መጠቀም ወንጀለኛን ሲዋሽ ለመያዝ እና የእምነት ክህደት ቃሉን ለማሰጠት የሚሞክር የፖሊስ መርማሪ ያስመስለዋል። “ቀደም ግን የተናገሩት አይደለም…” ከማለት ይቆጠቡ። ከማፋጠጥ ይልቅ ስለማዋሃድ የሚረዳ ዘዴ ነው።

ሐ. ስለመላሻቸው አንድምታ ጥያቄ ይጠይቁ።
ሰዎች በተለየ መልኩ ሳይገለጡ ለጥያቄው ምላሽ ሲሰጡ ወይም በጣም “አስተማማኝ” መልስ ሲሰጡ ምን ያደርጋሉ? ገላጭ ያልሆኑ መልሶችን በቀጥታ ከመቀበል ይልቅ የመልሱን አንድምታ በመጠየቅ ተጠያቂን በትክክል ለመረዳት ይሞክሩ። ለምሳሌ፦

ኒማ እርሻሽ በጣም ሥርዓታማ እና ጽዱ እንደሆነ ተናግረሻል። እንደዚህ አይነት እርሻ ስላለሽ ለአንቺ ምን ማለት ነው?

ኒማ እርሻው እንደምትፈልገው እንዲመስል ጠንክራ እንደምትሰራ እናውቃለን። ለእርሻዋ ገጽታ ምን መስዋዕትነት እንደምትከፍል ጥያቄ ሊሆንብዎት ይችላል።

ተከታዩ ጥያቄ ቀጣዩ ሊሆን ይችላል፦

ይሀ ሁሉ ነገር ለማድረግ ጊዜ እንዴት ታገኛለሽ?

ጥንቃቄ፡- ስለ ጥያቄው አንድምታ ሲጠይቁ መሪ ጥያቄዎችን ከመጠየቅ ይቆጠቡ። ይልቁንም፣ ስለሚናገሩት ነገር እና የምላሻቸው አንድምታን በንቃት ይከታተሉ።

ተከታይ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ሌሎች ምክንያቶች ሲኖሩ እርስዎ በሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ላይም ተጽእኖ ያሳድራሉ። ለምሳሌ፣ የሚከተሉትን ማድረግ ይቻላል፦

  • ተጠያቂው የምላሻቸውን ትርጉም እንዲያብራሩ ይጠይቁ።
  • ለማንሳት የሞከሩትን ነጥብ የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ይጠይቁ።
  • "ይህ ለ____ ምን ማለት ነው?" ብለው ይጠይቁ።
  • ተቃራኒ አስተያየቶችን ያንሱ እና ስለሱ ምን እንደሚያስቡ ይጠይቋቸው። (ለምሳሌ “አንዳንድ ሰዎች ጽዱ እና ሥርዓታማ እርሻን ማኖሩ ጊዜን ማባከን ነው ይላሉ…”)

ተከታይ ጥያቄዎች ጥሩን ቃለ መጠይቅ በጣም ጥሩ ቃለ መጠይቅ እንዲሆን የሚያደርጉት ናቸው። ጥሩ ተከታይ ጥያቄዎች የበለፀገ ዝርዝር፣ ባህሪ እና ስሜትን ያካተቱ ምላሾችን የሚያስገኙ ናቸው።

ሌሎች ነጥቦች

የተሻሉ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ከላይ ያሉት ምክሮች በማንኛውም ቃለ መጠይቅ ዓይነቶች ላይ ሊተገበሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ለአንድ ፖለቲከኛ ቃለ መጠይቅ ሲደረግ፣ ግልጽ እና ቀጥተኛ የሆኑ ጥያቄዎችን መጠየቁ ፖለቲከኛው ቀጥታ ምላሽ ከመስጠት እንዲሸሽ እድሉን አይሰጡትም። በቀጥታ ላለመመለስ ከመረጡ ደግሞ ጠያቂው የተለያዩ አማራጮች አሉት ይኖሩታል። “ጥያቄውን በሌላ መንገድ ላስቀምጥ…” ወይም “ለምን ጥያቄውን አልመለሱልኝም?” ማለት ይችላሉ። አጋፋጭ ቢሆንም ጠቃሚ ጥቅም አለው።

በጣም ግልጽ የሆኑ ምላሾችን ስለሚሹ ለፖለቲከኛ ወይም ባለሙያዎች ስለ ባህሪ እና ስሜት ጥያቄዎችን የመጠየቅ ዕድሉ አነስተኛ ሊሆን ይችላል። ሆኖም፣ ፖለቲከኞች እና ባለሙያዎችም ሰዎች እንደመሆናቸው የሚናገሩትን በደንብ እንዲረዱ ለአድማጮች ይረዳቸዋል።

የተሻሉ ጥያቄዎችን ስለመጠየቅ በሚመለከት መረጃዎችን ሌላ የት አገኛለሁ?

BBC Academy, undated. Ask clear, simple interview questions: Jeremy Paxman. https://rl.talis.com/3/lsbu/items/00BFC3CA-38DA-9642-EE3C-07D097D5D010.html

Columbia University, undated. Interviewing principles. http://www.columbia.edu/itc/journalism/isaacs/edit/MencherIntv1.html

Davis, Richard, 2014. Tactics for Asking Good Follow-up Questions. https://hbr.org/2014/11/tactics-for-asking-good-follow-up-questions

Farm Radio International, 2016. How to conduct an effective interview. https://training.farmradio.fm/how-to-conduct-an-effective-interview/

Farm Radio International, 2017. Interviewing experts: Best practices for broadcasters and experts. https://training.farmradio.fm/how-to-interview-experts-best-practices-for-broadcasters-and-experts/

Halbrooks, Glenn, 2019. Conducting a good television interview. https://www.thebalancecareers.com/tv-interview-tips-for-news-media-professionals-2315424

MediaCollege.com, undated. Leading Questions. https://www.mediacollege.com/journalism/interviews/leading-questions.html

Pizarro, A. G., 2015. Qualitative Interviewing: 3 Mistakes to Avoid in Question Formulation. http://simplyeducate.me/2015/02/08/qualitative-interviewing-3-mistakes-to-avoid-in-question-formulation/

ምስጋና

አዘጋጅ፦ ዲክ ሚለር፤ የፍሪላንስ የሬዲዮ ፕሮዲዩሰር፣ አሰልጣኝ እና የቀድሞ የሲቢሲ ሬዲዮ ዘጋቢ ፊልም አዘጋጅ፣ የላቀ ዶክመንተሪ አውደ ጥናት፣ የኪንግስ ኮሌጅ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት መምህር።

ይህ ግብአት የተደገፈው የአረንጓዴ ፈጠራ ማዕከል ፕሮጀክትን ተግባራዊ በሚያደርገው ከዶይቸ ጌሴልስቻፍት ፉር ኢንተርናሽናል ዙሳምሜናርቤይት ጂኤምቢኤች (ጂ አይ ዜድ) በተገኘ እርዳታ ነው።

Translation thanks to Global Affairs Canada