የራዲዮ ጋዜጠኞች ከቢሮ ውጭ እንዴት መሥራት እንደሚችሉ

አንድ የራዲዮ ጋዜጠኛ ከቢሮ ውጭ እንዴት መሥራት እንደሚችል ማወቅ ምን ይጠቅመዋል?

አንዳንድ ጊዜ የራዲዮ ጋዜጠኞች ቦታው ላይ በመገኘት ወይም ጉዳዩ ላይ ተሳታፊነት ያላቸውን ሰዎች በገጽ በማግኘት መዘገብ ላይችሉ ይችላሉ፡፡ እንደ ኮቪድ-19 አይነት ወረርሽኝ ሲፈጠር እና መንግስታት የአካላዊ እርቀት ድንጋጌዎች ሲያወጡ እና በቤታችን ካሉ ሰዎች ውጭ ከሌሎች ሰዎች ጋር ቢያንስ የአንድ ሜትር እርቀት እንድንጠብቅ ስንገደድ በአካል ተገኝቶ እና ተገናኝቶ መዘገብ ሊያስቸግር ይችላል፡፡

የዜና ተቋማት ግን በብዙ አገሮች በጣም አስፈላጊ ተቋማት ናቸው፡፡ ስለዚህ የራዲዮ ጋዜጠኞች ከእርቀት ሆነው ራሳቸውን ከጉዳት በመጠበቅ መዘገብ መቀጠል ይጠብቅባቸዋል፡፡

“አስፈላጊ አግልግሎቶች” ምንድን ናቸው፣ ከራዲዮ ጋዜጠኞች ጋርስ ምን ያገናኛቸዋል?

አስፈላጊ አገልግሎቶች ምን እንደሆኑ ለመወሰን የተለያዩ መንግስታት የተለያዩ መስፈርቶች ሊኖሯቸው ይችላሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ አስፋላጊ አገልግሎቶች ውስጥ የሚከተሉት ይካተታሉ፡- ጤና አገልግሎት፣ ምግብ፣ ሕግ ማስከበር፣ አንዳንድ የችርቻሮ አግልግሎቶች፣ እና ለእለታዊ ኑሮ በጣም አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ የንግድ እንቅስቃሴዎች፡፡ ሰዎች ትክክለኛ እና ትኩስ መረጃ ማግኘት ስለሚያስፈልጋቸው የራዲዮ እና ቴሌቪዝን አግልግሎት በብዙ አገሮች አስፋላጊ አገልግሎት ሆኖ ይቆጠራል፡፡ ሰዎች መረጃ በራዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ኢንተርኔት፣ ህትመት እና በሌላም ሜዲያ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለዚህ የራዲዮ ጣቢያዎች እና ጋዜጠኞች ለአፍሪካ አርሶ አደሮች እና ቤተሰቦቻቸው ጠቃሚ የሆነ ወቅታዊ እና ትክክለኛ መረጃ የማቅረብ ሚናቸው ከምንጊዜውም በላይ ከፍተኛ ነው፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ ወቅት የራዲዮ ጋዜጠኞች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለማወቅ የሚከተለውን ሊንክ ተጭናችሁ አንብቡ፡- Broadcaster how-to guide on planning and producing effective emergency response programming (COVID-19)፣ በኮቪድ-19 ወረርሺኝ ወቅት ደግሞ አንድ የራዲዮ ጋዜጠኛ ራሱን እንዴት መጠበቅ እንዳለበት ለማወቅ ይህንን ሊንክ ተጫኑ፡- Staying safe as a broadcaster during the COVID-19 pandemic.

How your station can help prevent the spread of COVID-19 and keep your listeners safe

ከርቀት ሆኖ መሥራት ተግዳሮቶቹ ምንድን ናቸው?

የሥራ ቦታን ከራዲዮ ጣቢያ ወደ ቤት ወይም ሌላ ከቢሮ ውጭ ወዳለ ቦታ መቀየር ሊያስቸግር ይችላል፤ አብዛኛው ኢንተርኔት ላይ የሚገኘው ምክር በአፍሪካ ገጠራማ አካባቢዎች የሚሠሩ የራዲዮ ጋዜጠኞችን ጥያቄዎች ስለማይመልስ የበለጠ አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ከተግዳሮቶቹ መካከል የስልክ እና የኢንተርኔት ግንኙነት አስተማማኝ አለመሆኑ፣ ቴክኒካል ችግሮችን መፍታት የሚችሉ ባለሙያዎች አለመኖር፣ ውጥረትን (ጭንቀትን) እና የአይምሮ ጤንነትን መቆጣጠር አለመቻል፣ ከቤት ውስጥ ሲሠሩ በቤተሰብ አባላት መረበሽ፣ እና መደበኛ ፕሮግራሞች እና የስርጭት መንገዶች ሲቀየሩ ታማኝ ደምበኞችን ይዞ ማቆየት አለመቻል ይገኙበታል፡፡ ደግነቱ ግን ራዲዮ ለተለያዩ ሁኔታዎች በቀላሉ የሚመቻች ስለሆነ ጋዜጠኞቹ በቀላሉ አሠራራቸውን ከራሳቸው ጋራ ማመቻቸት ይችላሉ፡፡ ይህ ሰነድ በርቀት ሆናችሁ የራዲዮ ፕሮግራም እንዴት ማሰራጨት እንደምትችሉ ያስረዳችኋል፡፡ ስለሚከተሉት ነገሮ ች ትማራላችሁ – በጀት አዘገጃጀት፣ ጥሩ የኢንተርኔት ኮኔክሽን ለማግኘት ማድረግ ያለባችሁ ኢንቬስትምነት፣ ቴክኒካዊ ችግሮችን ለመፍታት ከሥራ ባልደረቦቻችሁ ጋር በኢንተርኔት እንዴት እንደምትገናኙ፣ የአይመሮ ጤንነታችሁን እንዴት መጠበቅ እንደምትችሉ እና አድማጮቻችሁን የሚስቡ፣ የሚያስተምሩ እና የሚያዝናኑ የራዲዮ ፎርማቶችን እንዴት እንደመትጠቀሙ ትማራላችሁ፡፡

በርቀት ሆኜ እንዴት አድርጌ ውጤታማ የፕሮግራም ስርጭት ማድረግ እችላለሁ?( ስለነዚህ እና ሌሎች ጉዳዮች ከታች ካለው ዝርዝር ክፍል ተጨማሪ መረጃ ታገኛላችሁ፡፡)

 1. በርቀት ለመሥራት የሚያስችሏችሁን መሣርያዎች እና ቁሳቁስ ሰብስቡ
 2. ቃለ መጠይቆችን በርቀት አድርጉ
 3. አንዳንድ የራዲዮ ፎርማቶችን መጠቀም አቁሙ
 4. ብዙ በማያስቸግሩ የራዲዮ ፎርማቶች ተለማመዱ
 5. ከባለሙያዎች ጋር በፊት ያደረጋችኋቸውን ቃለ መጠይቆች እና ያለፉ ፕሮግራሞቻችሁን በድጋሚ ተጠቀሙ
 6. ባንድ ጊዜ የሚሠሩ ሥራ ባልደረቦችን ቁጥር ቀንሱ
 7. ስብሰባዎችን በርቀት አካሂዱ
 8. የመረጃ ምንጮችን ለማግኘት እና የተቀረጹ ድምጾችን በጋራ ለመጠቀም ተባበሩ
 9. ከቤት ሆኖ ለመሥራት ጥሩ የኢንተርኔት ኮኔክሽን እንዲኖራችሁ አድርጉ
 10. ፕሮግራሞቻችሁን ለማዘጋጀት የፋርም ራዲዮ ኢንተርናሽናል መረጃዎችን ተጠቀሙ

ዝርዝር

1. በርቀት ለመሥራት የሚያስችሏችሁን መሣርያዎች እና ቁሳቁስ ሰብስቡ

በርቀት ለመሥራት የሚያስፈልጓችሁ መሣርያዎች ዝርዝር ከዚህ በታች ቀርቧል፡፡ በኮቪድ-19 ችግር ወቅት ወደቤታችሁ የምታመጡትን ማንኛውንም መሣርያ ከጀርም ማጽዳት እንዳትዘነጉ፤ ካመጣችሁም በኋላ ሁል ጊዜ አጽዷቸው፡፡

 • መቅረጸ-ድምጽ:- በገጽ ተገናኝታችሁ የምትቀርጹት ቃለ መጠይቅ ባይኖርም መቅረጸ ድምጻችሁን የስልክ ንግግር፣ ቪዲዮዎች እና ሌሎችን በድምጽ ተቀርጸው ያሉ ሰነዶችን ለመቅዳት ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ፡፡ በመቅረጸ ድምጻችሁ ከፍተኛ ጥራት ያለው ድምጽ ለመቅዳት የሚከተለውን የፋርም ራዲዮ ሰነድ አንብቡ፡- BH2 on Basic recorder settings.
 • ስማርት ፎን ወይም ታብሌት፡- ዋትስአፕ፣ ሰካይፕ ወይም ዙም በመጠቀም ቃለ መጠይቅ ለማካሄድ እና ለመቅረጽ በመቅረጸ ድምጽ ፋንታ ስማርት ስልኮቻችሁን ወይም ታብሌት መጠቀም ትችላላችሁ፡፡ ላፕቶፕ ወይም ዴስክቶፕ ኮምፒዩተር ከሌላችሁ ስማርት ስልኮች እና ታብሌቶችን በኢንተርኔት መረጃ ለማሰባሰብ ልትጠቀሙባቸው ትችላላችሁ፡፡
 • ላፕቶፕ:- ላፕቶፕ ወይም ዴስክቶፕ ኮምፒዩተር ቤታችሁ ካላችሁ ኢንተርኔት ላይ መረጃ ለመፈለግ እና የድምጽ አርትኦት/ኤዲቲንግ ሶፍትዌር በቀላሉ ለመጠቀም ትችላላችሁ፡፡ የድምጽ አርትኦት ሶፍትዌር ብዙም ተጠቅማችሁ የማታውቁ ከሆነ ይህን ሊንክ በመጫን የፋርም ራዲዮን መረጃ አንብቡ፡- BH2 on recommended audio editing tutorials.
 • አንድ መደበኛ የሥራ ቦታ አመቻቹ፡- ይህን በማድረግ የተሻለ ትኩረት ለማግኘት እና የሥራ እና የቤት ሕይወታችሁን ለመለየት ያስችላችኋል፡፡ ሥራችሁን የምትሠሩት በጥቂት እቃዎች እና በጠባብ ቦታ ላይ ቢሆንም እንኳን በደምብ ለመደራጀት እንዲመቻችሁ ቤት ውስጥ፣ ግቢ ውስጥ ወይም ሌላ የማትረበሹበት የሥራ ቦታ ለማመቻቸት ሞክሩ፡፡ ዴስክ እና ወንበር ከሥራ ቁሳቁሶቻችሁ ጋር ብቻ ብታመቻቹ እንኳን በደምብ የመደራጀት መንፈስ ይፈጥርላችኋል፡፡
 • የስልክ ሒሳብ፡- ወደ ውጭ ለመውጣት እንዳትገደዱ የሞባይል ሒሳባችሁን በደምብ ሙሉ፡፡ ከቢሮ ውጭ ሆናችሁ ስትሠሩ የሚያጋጥማችሁ ወጭ እንዴት እንደሚሸፈን ከሥራ ኃላፊዎቻችሁ ጋር መጀመርያ ተወያዩና የስልክ ወጫችሁ ምን ያህል እንደሆነ መዝግቡ፡፡ አለቆቻችሁ ከተስማሙ በጀትና የሒሳብ መጠየቂያ አስገቡ፡፡
 • የስልክ ጥሪዎች ወደናንተ ስልክ እንዲዛወሩ ማድረግ፡- ጣቢያችሁ የስቱዲዮ ስልክ ካለው የስልክ ጥሪዎች ወደ ግል ስልካችሁ እንዲዛወሩ/እንዲተላለፉ ማድረግ ይቻል እንደሆነ አጣሩ፡፡ ካልተቻለ ጣቢያ ውስጥ ሆኖ ጥሪ የሚቀበል እና የሚመዘግብ አንድ ሰው ይመደብ፤ ጣቢያ ውስጥ በምትሆኑ ጊዜ አካላዊ እርቀታችሁን ጠብቁ፡፡
 • እስክርቢቶ፣ ወረቀት፣ ካልኩሌተር፣ ወዘተ፡- የቢሮ መጠቀሚያ ግብኣቶችን ወደ ቤታችሁ መውሰድ ትችሉ እንደሆነ አለቆቻችሁን ጠይቁ፡፡ ወይም ከቤት ለመሥራት የሚያስፈልጓችሁን እቃዎች ለመግዛት በጀት አዘጋጅታችሁ አስገቡ፡፡

ሥራ ቦታ ላይ አካላዊ እርቀት እንዲኖር እና ከቤት ሆነው የሚሠሩ ሠራተኞችን ለመደገፍ የሥራ ኃላፋዎች የሚከተሉትን ማድረግ ይችላሉ፡-

 • የስልክ እና የኢንተርኔት ግንኙነት ችግር ሲያጋጥም ምክር የሚሰጥ እና ከቤት ሆነው ለሚሠሩ ሰዎች የቴክኒክ ድጋፍ የሚሰጥ አንድ ሰው መድቡ፡፡ ይህ የሥራ ባልደረባ ከአገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶችም ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ሊረዳ ይችላል፡፡
 • የዝግጅት ክፍል የሥራ ባልደረቦች እና የሥራ ሃላፊዎች የፕሮግራሙ ተከታታዮች እያዳመጡ መሆን አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ ከአድማጮች ጋር በስልክ ለመገናኘት ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ በወረርሽኙ ወቅት በሙሉ ግብረ መልስ እና ጥቆማ እንዲሰጡ ጠይቋቸው፡፡ ሴት አድማጮችንም ለማግኘት ሞክሩ፡፡ አንዳንድ ሴቶች ራዲዮ እና ስልክ የማግኘት እድላቸው ውስን ነው፡፡ ሌሎች አድማጮች እነዚህን ሴቶች (በቤተሰባቸው ውስጥ ያሉትን ጨምሮ) እንዲያገኟቸውና ድጋፍ በማቅረብ ከራዲዮ ጣቢያው ጋር መስተጋብር እንዲኖራቸው ያግዟቸው፡፡
 • የሥራ ሃላፊዎች ጋዜጠኞቻው በኮቪድ-19 በተጠቁ አካባቢዎች ውስጥ ደህንነታቸውን መጠበቅ እንዲያውቁ እና በወረርሽኙ ወቅት ዘገባ መሥራት የሚችሉባቸውን ምርጥ ተሞክሮዎች እንዲያውቁ መመርያ ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ በጣም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ጋዜጠኞቹ ማንንም ሰው በአካል አግኝተው ማነጋር የለባቸውም፤ ያን ማድረግ ሲኖርባቸውም ጭንብል እና ጓንት ማድረግ እና ቢያንስ አንድ ሜትር እርቀው መቆም አለባቸው፡፡ ጋዜጠኞቹ ከቤት ሆነው መሥራት ካልቻሉ ስቱዲዮ ውስጥ በሚቀመጡበት ሰዓት ሁሉ ጭንብል መልበስ አለባቸው፡፡ እነዚህ መመርያዎች በዋትስኣፐ በመጠቀም፣ በርቀት ስብሰባ እና ጣቢያው ውስጥ ግርግዳ ላይ በመለጠፍ መሰራጨት አለባቸው፡፡

2. ቃለ መጠይቆችን በርቀት አድርጉ

በጣም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ቃለ መጠይቅ ከምታደርጉለት ሰው ጋር በአካል አትገናኙ፡፡ በዚያ ፋንታ በስልክ ቀጥታ ቃለ መጠይቅ አድርጉ ወይም ቃለመጠይቁን መጀመርያ ቅረጹትና ጥራት እንዲኖረው ኤዲት አድርጉት፡፡ ብዙ ስልኮች የስልክ ጥሪ መቅረጫ የላቸውም፤ ስለዚህ ስልኩን ሰፒከር (ላውድ) ላይ አድርጉና መቅረጸ ድምጽ አጠገብ አስቀምጣችሁ ቃለመጠይቁን ቅረጹ፡፡ ወይም ስካይፕ ከተጠቀማችሁ ስልክና ቪዲዮ በቀጥታ በመተግበርያው መቅረጽ ትችላላችሁ፡፡ ልክ ቃለ መጠይቁን እንደጀመራችሁ “Start recording” የሚለውን ቁልፍ ተጫኑ፡፡ ከዘጋችሁ በኋላ የቀረጻችሁት ድምጽ እና ምስል ለ30 ቀናት የስካይፕ መስኮት ውስጥ ታገኙታላችሁ፡፡ እንዳይጠፋባችሁ 30 ቀን ከማለፉ በፊት አውርዳችሁ ሴቭ አድርጉ፡፡

1: ስካይፕ ዴስክቶፕ

 

Image 1: Skype desktop

 

2: ስካይፕ ሞባይል

 

Image 2: Skype mobile

 

በርቀት/በአካል ሳትገናኙ ቃለ መጠይቅ በምታደረጉበት ጊዜ ከዚህ በታች ያሉትን ሃሳቦች መጠቀም ትችላላችሁ፡፡ ቃለ መጠይቅ የምታደርጉለት ሰውም እነዚህን ምክሮች እንዲጠቀም ማድረግ ትችላላችሁ፡-

 • የስልካችሁን ኖቲፊኬሽን አጥፉ፤ የምታነጋግሩት ሰውም እንዲያጠፋ ንገሩ፡፡ ይህን ስታደርጉ ያልተጠበቁ ድምጾች እንዳይረብሽዋችሁ ታደርጋላችሁ፡፡
 • መቅረጽ ከመጀመራችሁ በፊት የድምጽ መጠኑን አረጋግጡ፡፡ የምታነገጋግሩትን ሰው ጸጥ ወዳለ ቦታ እንዲቀይር መንገር ሊያስፈልጋችሁ ይችላል፡፡ ቃለ መጠይቁ እስኪያልቅ ድረስ እናንተም ጸጥ ያለ ቦታ ውስጥ መሆን ያስፈልጋችኋል፡፡
 • ቃለ መጠይቅ እያደረጋችሁ ከቦታ ቦታ አትንቀሳቀሱ፡፡ ኔትወርክ ሊያቋርጥባችሁ ይችላል፣ ስትነጋገሩም ትንፋሻችሁ ሊቆራረጥባችሁ ይችላል፡፡
 • የማይፈለግ ድምጽ ሊገባባችሁ ስለሚችል ድምጽ እየቀረጻችሁ ስልካችሁን ወይም ኮምፒዩተራችሁን አታንፏቁ፡፡
 • ቃለ መጠይቅ እያደረጋችሁ በስልካችሁ ወይም በኮምፒዩተራችሁ ሌላ ሥራ አትሥሩ (ለምሳሌ ኢሜይል ማየት ወይም አጭር የጽሑፍ መልእክት መላክ)
 • ተቀርጾ ኋላ የሚተላለፍ ቃለ መጠይቅ እየቀረጻችሁ ከሆነ ቃለ መጠይቁን ስትጨርሱ ተጠያቂው ዋና ዋና ነጥቦቹን በአጭሩ እንዲያቀርብላችሁ ጠይቁ፡፡ በፕሮግራማችሁ የምትጠቀሙበት ጥሩ እና አጭር ሳውንድ ባይት ይሆናችኋል፡፡ ቀጥታ በሚተላለፍ ቃለ መጠይቅ ግን ይህን ጥያቄ አታቅርቡ፤ ረጅም መልስ ከተሰጣችሁ ቀጣዩን ፕሮግራም ሊያዘገይባችሁ ይችላል፡፡
 • ዘግጁና ንቁ ሁኑ፤ በደምብ አዳምጡ፡፡ የአንድን ሰው አካላዊ እንቅስቃሴ ሳያዩ ቃለ መጠይቅ ማድረግ ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡ ማሃል ማሃል ላይ ቆም ለማለትና ትንሽ ጸጥታ እንዲኖር አድርጉ፣ ነገር ግን ተከታታይ ጥያቄዎቻችሁን አዘጋጅታችሁ ጠብቁ፡፡ ረጅም ዝምታ እንዳይኖር አድርጉ፤ ተጠያቂው ስልኩን ያቋረጣችሁ ወይም መናገር እንዲቀጥል የፈለጋችሁ ሊመስለው ይችላል – ሁለቱም ቃለ መጠይቁን መስመር ሊያስለቅቁ ይችላሉ፡፡

ልክ እንደማንኛውም ቃለ መጠይቅ ከቤት ሆናችሁም ሆነ በገጽ ብታደርጉት የጥያቄዎች ዝርዝር ማዘጋጀት ጠቃሚ ነው፡፡ ማንኛውንም የተወሳሰበ ሃሳብ ወይም ርዕሰ ጉዳይ ወይም ግልጽ ያልሆነ መልስ እንዲያብራራ ቃለ መጠይቅ የምታደርጉለትን ሰው ለመጠየቅ አትፍሩ፡፡ እናንተ ግራ ከገባችሁ አድማጮቻችሁም ግራ ሊገባቸው ይችላል! ቃለ መጠይቅ ከምታደርጉለት ሰዉ ጋር በደምብ የታሰበባቸው እና ጥናት የተደረገባቸው ጥያቄዎች በመጠየቅ እና መልሶቹን በጥንቃቄ በማዳመጥ በአክብሮት ተነጋሩ፡፡ ስለ ጾታ እኩልነት ለምሳሌ አሁን በኮቪድ-19 ምክንያት እየጨመረ ስለመጣው የቤት ውስጥ ጥቃት እና ሴቶች ግምባር ቀደም ሠራተኞ ስለሆኑ ለኮቪድ-19 ስላላቸው ተጋላጭነትም ጥያቄዎች አቅርቡ፡፡ ጥልቅ እና ሰፊ ጥያቄዎች እየጠየቃችሁ ርዕሰ ጉዳያችሁን ግን ጠብቁ፡፡ ካስፈለገ በቃለ መጠይቁ ሂደት የተወያያችሁት ጉዳይ ትክክለኛነቱን እና ሚዛናዊነቱን ሳታሳጡ ቃለ መጠይቁን ዋናው ነገር ላይ እንዲያተኩር አድርጋችሁ በአርትኦት ማሳጠር ትችላላችሁ፡፡ የሚቀርበው መረጃ የሴቶችን እና የወንዶችን የተለያዩ ፍላጎቶች የሚያካትት እንዲሆን አድርጉ፡፡

የድምጽ አርትኦት የታሪካችሁን ትኩረት እና የአድማጮቻችሁን የመረጃ ፍላጎት መሰረት በማድረግ መግባት እና መውጣት ያለባቸውን ክፍሎች መምረጥ ያካትታል፡፡ በሞባይል የቀረጻችሁትን ቃለ መጠይቅ ስታርሙ ልክ በገጽ እንደተደረገ ቃ ምልልስ “ኧም” እና “አአ” የሚል ድምጾችን እና ሌሎችንም አላስፈላጊ ክፍሎች ቆርጣችሁ በማውጣት ቃለ መጠይቁ አጭር እና ግልጽ እንዲሆን ታደርጋላችሁ፡፡ ሙሉውን ቃለ መጠይቅ ግን መልሳችሁ መስማት አለባችሁ፤ የምታስቀሩትን እና ቆርጣችሁ የምታወጡትን ለመለየት ቃለ መጠይቃችሁ ትኩረቱ ምን ላይ እንደሚሆን ወስኑ፤ የዝግጅት ፎርማት ምረጡ – ለምሳሌ አጫጭር ክሊፖች/ቅንጥቦች አንድ ላይ ተጋጥመው፣ ወይም ሙሉ ቃለ መጠይቅ፣ ወይም በአንድ ድምጽ የሚደረግ ትረካ ማድረግ ትችላላችሁ፡፡ የተቀረጸውን ድምጽ ተከታታይነት ስሜት እንዲሰጥ አድርጋችሁ ቅደም ተከተሉን አስተካክሉ፡፡ እነዚህን ደረጃዎች መከተል ከቤት ሆናችሁ ጠቃሚ፣ ውጤታማ እና አዝናኝ የሆነ የራዲዮ ፕሮግራም ለማዘጋጀት ይረዷችኋል፡፡

ለተጨማሪ ዕውቀት የሚከተሉትን የፋርም ራዲዮ መመርያዎች አንብቡ፡- audio editing እና interviewing techniques.

3. አንዳንድ የራዲዮ ፎርማቶችን መጠቀም አቁሙ

አንዳንድ የራዲዮ ፎርማቶች በአካል መገናኘተ ስለሚያስፈልጋቸው በኮቪድ-19 ወቅት ለደህንነት አስቸጋሪ ናቸው፡፡ በአካል መገናኘት የቫይረሱን የመሰራጨት ዕድል ይጨምራል፡፡ ስለዚህ አጫጭር ዶከዩመንታሪዎችን፣ የሕዝብ አስተያየቶችን እና ብዙ ሰዎች ባንድ ላይ ሆነው የሚጫዎቷቸውን ጫወታዎች የአካላዊ እርቀት መመርያ እስከሚነሳ ድረስ መስራት አቁሙ፡፡

4. ብዙ በማያስቸግሩ የራዲዮ ፎርማቶች ተለማመዱ

ራሳችሁን እና ሌሎችን ለጉዳት ሳታጋልጡ አዝናኝ እና አስተማሪ የሆኑ የራዲዮ ፎርማቶችን ተጠቀሙ፡፡ ጥቂት ምሳሌዎች ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል፡-

1. የስልካችሁን ኮንፈረንስ ኮል ፊቸር በመጠቀም ብዙ ሰዎችን ባንድ ጊዜ ደውሉላቸውና የፓነል ውይይት አድርጉ : የሞባይላችሁን ወይም የመስመር ስልካችሁን ኮንፈረንስ ኮል አማራጭ በመጠቀም ብዙ ሰዎችን የፓነል ውይይት ተሳታፊዎች እንዲሆኑ መጋበዝ ትችላላችሁ፡፡ ከቤት ሆናችሁ በምትሠሩበት ሰዓት በጃችሁ ላይ ያለውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ተወያዮቹን በስካይፕ፣ ጉግል ሃግአውትስ ወይም ዙም በመጠቀም ልትሰበስቧቸው ትችላላችሁ፡፡ የቀጥታ ፕሮግራሙን ማስተላለፍ ከመጀመራሁ በፊት ተወያዮቹ በአካል ተገናኝተው ላያውቁ ስለሚችሉ እራሳቸውን እያስተዋወቁ አንዳንድ ነገር እንዲናገሩ የሙከራ ውይይት አድርጉ፡፡ ፓነላችሁ እኩል ሴቶች እና ወንዶች እንዲኖሩት አድርጉ፣ የጾታ እኩልነት ባለሙያም ለማሳተፍ ሞክሩ፡፡

2. ቴፕ ቶክ : ይህ የአተራረክ ፎርማት በፕሮግራሙ አቅራቢ እና በሪፖርተሩ መካል የሚደረግ ውይይት ነው፡፡ ይህ አቀራረብ በከፊል ቀጥታ የሚደረግ ቃለ ምልልስ ሲሆን በከፊል ደግሞየተቀረጸ ድምጽ ይገባበታል፡፡ አቅራቢው ሪፖርተሩን ሲጠይቀው ሪፖርተሩ ከመልሱ ጋራ የቀረጻቸውን የድምጽ ክሊፖች/ቅንጥቦች ያጫውታል፡፡ ቴፕ ቶክ ቶሎ መዘጋጀት ይችላል፤ አጭር ወይም የበለጠ ገላጭ እንዲሆን ረጅም መሆን ይችላል፡፡ ቃለ መጠይቁ አስቀድሞ የተቀረጸ ቢሆንም እንኳን የሪፖርተሩን ድምጽ በቀጥታ ስርጭት ያስገባሉ፡፡

3. የስልክ ጥያቄዎች : የራዲዮ ጥያቄዎች በጣም አዝናኝ ከመሆናቸውም በላይ አድማጮችን ለመሳተፍ ያበረታታሉ፡፡ ቀላሉ እና ውጤታማው የራዲዮ ጥያቄ አውነት ሃሰት ወይም ምርጫ ጥያቄዎችን መጠየቅ ነው – ሁለቱንም መቀላቀል ይቻላል፡፡ አብላጫ ጥያቄዎችን የሚመልሰው ደዋይ አሸናፊ ይሆናል፡፡ ጥያቄ ለማቅረብ የተለያዩ ዘዴወች አሉ፡፡ አንደኛው ለሁሉም ተሳታፊዎች አንድ አይነት ጥያቄ አቅርቦ የቀደመ እንዲመልስ ማድረግ ነው፡፡ ሌላው ለያንዳንዱ ተሳታፊ የራሱ ጥያቄ ጠይቆ ለመመለስ የሰኣት ገደብ ማስቀመጥ ነው፡፡ ጥያቄውን በምንም መልኩ ብታቀርቡ አሸናፊው ከራዲዮ ጣቢያው ትንሽ ሽልማት ያገኛል ወይም የውድድሩ አሸናፊ የሚል ክብር ይሰጠዋል፡፡ አካላዊ እርቀትን ለመጠበቅ እንዲያስችል አስቀድመው የተመረጡ ተሳታፊዎችን ልትጠሩ ትችላላችሁ ወይም አድማጮች እየደወሉ እንዲመልሱ ማድረግ ትችላላችሁ፡፡ ሴቶችም እንዲሳተፉ የሚያስችሉ አካሄዶችን ተከተሉ፤ ለምሳሌ ሴቶች ብቻ የሚደውሉበት የስልክ መስመር በማዘጋጀት፣ እንዴት መሳተፍ እንደሚቻል ተጨማሪ መረጃ በማቅረብ እና የሴቶችን አስተያየቶች እና መልሶች ከወንዶቹ እኩል ለመስለማት ያላችሁን ፍላጎት በመግለጽ ማበረታታት ትችላላችሁ፡፡

4. የዋትስአፕ የድምጽ ማስታወሻ፡- በአካል ሄዳችሁ የሕዝብ አስተያየት ከመቅረጽ በተሻለ ደግሞ አድማጮቻችሁ በዋትስአፕ የድምጽ መልእክት እንዲልኩላችሁ ጠይቋቸው፡፡ በዋትስአፕ ድምጽ ለመቅረጽ ከኪቦርዱ (መጻፊያው) በሰትቀኝ ያውን የማይክሮፎን ምስል ጫን አድርጋችሁ ያዙና ድምጻችሁን ቀርጻችሁ ስትጨርሱ ልቀቁት፡፡ ከዚያ ቀሰቱን ነካ ስታደርኩት ልትልኩለት ወደ መረጣችሁት ስልክ ይሄዳል፡፡ የድምጽ መልእክቱን የሚቀበለው የራዲዮ ጋዜጠኛ የድምጽ መልእክቱን አውርዶ ሴቭ ማድረግ ካስፈለገም ኤዲት ማድረግ ይችላል፤ ከዚያ ድምጹ በአየር ላይ ይተላለፋል፡፡

5. ድራማዎች፡- የአካላዊ እርቀት መመርያዎችን ሳንጥስ የራዲዮ ድራማ ማዘጋጀት ይቻላል፡፡ እያንዳንዱ ተዋናይ የራሱ ማይክሮፎን ሊኖረው እና ቢያንስ በአንድ ሜትር እርቀት ሊቆም ይገባል፡፡ ተዋንያኑ የእጅ ጓንት እና ከተቻለ የፊት መሸፈኛ ጭንብል መልበስ አለባቸው፡፡ ሰፊ ክፍል ለማመቻት ሞክሩ (ለምሳሌ አንድ ባዶ መማርያ ክፍል ወይም የመሰብሰቢያ አዳራሽ)፣ ካልሆነም ከቤት ውጭ ብታደርጉት ለአንዳንዶች ትዕይንቶች የተፈጥሮ እና የአካባቢ ድምጽ መቅረጽ ያስችላችኋል፡፡ እነዚህ ክልከላዎች አጠር እና ቀለል ያሉ ድራማዎችን እንድትቀርጹ ሊያስገድዷችሁ ቢችሉም በተጓዳኝ ግን የተለያዩ ፎርማቶችን አየር ላይ በመጠቀም ስለ ኮቪድ-19 አስፈላጊ መረጃዎችን በማስተላለፍ የአድማጮችን ትኩረት ለመሳብ ሊረዷችሁ ይችላሉ፡፡

ረዘም ያለ የፎርማቶች ዝርዝር ከዚህ ሊንክ ማግኘት ትችላላችሁ፡- BH2 on radio formats.

5. ከባለሙያዎች ጋር በፊት ያደረጋችኋቸውን ቃለ መጠይቆች እና ያለፉ ፕሮግራሞቻችሁን በድጋሚ ተጠቀሙ

ከቤት ወይም ከስቱዲዮ ሆናችሁ አዳዲስ ቀረጻዎችን ለማድረግ ሊቸግራችሁ ይችላል፣ ስለዚህ አንዳንድ ከዚህ በፊት የሠራችኋቸውን ሥራዎች በድጋሚ ለመጠቀም ፋይላችሁን ፈትሹ፡፡ አስተማማኝ የሆኑ ባለሙያዎችን ወቅታዊ መረጃ እንዲሰጧችሁ ጠይቋቸው፤ አዳዲስ ቃለ መጠይቅ የሚደረግላቸው ሰዎችን ግን በአካል አታግኙ፡፡ አሮጌ ቃለ መጠይቅ በድጋሚ ስትጠቀሙ ወይም ስትጠቅሱ ለአድማጮቻችሁ አዲስ ቃለ መጠይቅ እንዳልሆነ ግልጽ አድርጉ፤ ያነጋገራችኋቸውንም ሰዎች አግኙና አዲስ መረጃ ለማግኘት ሞክሩ፡፡ ሃሳባቸውን ቀይረው ከሆነ ወይም ልታነጋግሩት የሚገባ አዲስ ባለሙያ ካለ ጠይቋቸው፡፡ መረጃው ካልተቀየረ በርዕሰ ጉዳዩ ዙርያ ለአድማጮች ጠቃሚ የሆነ ተጨማሪ ነገር ካለ ጠይቋቸው፡፡ እነዚህን አዳዲስ ዝርዝር መረጃዎች ከያዛችሁ በኋላ ቃለ መጠይቁ ሲያልቅ በድጋሚ አቅርቧቸው እና አድማጮቻችሁን እንደገና ቃለ መጠይቁ ከተቀረጸ ቆየት ያለ እንደሆነ ተናገሩ፡፡

6. ባንድ ጊዜ የሚሠሩ ሥራ ባልደረቦችን ቁጥር ቀንሱ

ከሥራ ሃላፊዎቻችሁ ጋር ራዲዮ ጣቢያው ውስጥ የአካላዊ እርቀት እንዴት መጠበቅ እንደሚቻል ተነጋገሩ፡፡ ለምሳሌ ድምጽ መቅረጫው ክፍል ውስጥ በአንድ ጊዜ አንድ ሰው ብቻ ሊገባ ይችላል፤ ፊት ለፊትም ላይ አንድ እንግዳ ተቀባይ ብቻ ሊኖር ይችላል፡፡ ራዲዮ ጣቢያው ለሕዝብ ክፍት መሆን የለበትም፤ አድማጮችም በአካል ከመምጣት ይልቅ ስልክ እንዲደውሉ መበረታታት አለባቸው፡፡ በተቻለ መጠን የራዲዮ ጋዜጠኞች ከቤታቸው ሆነው እንዲሠሩ መበረታታት አለባቸው፡፡ ከቤት ሆነው መሥራት የማይችሉት ከሌሎች ሠራተኞች ጋራ አካላዊ ንክኪን ለመቀነስ በተሰባጠረ ሺፍት ለመሥራት መሞከር አለባቸው፡፡

ጣቢያው ውስጥ ያሉ ሰዎች በሁሉም ሰዓት ጭንብል መልበስ አለባቸው፤ ጠረጴዛቸውን፣ ኮምፒዩተራውን፣ ስልካቸውን እና ማይክሮፎናቸውን ከ60% በላይ ኢታኖል ወይም 70% አይሶፕሮፓኖል ያለው ሳኒታይዘር በመጠቀም ከጀርም ማጽዳት አለባቸው፡፡ ፕሮግራም አቅራቢዎች እና ቴክኒሻኖች ስቱዲዮ ውስጥ ያሉ ሁሉንም መሳርያዎች እና ጠረጴዛቸውን ጨምሮ ማንኛውንም የሚነኩትን እቃ ከጀርም በማጽዳት የእራሳቸውን እና የሌሎችን ደህንነት መጠበቅ አለባቸው፡፡

አካላዊ እርቀት ደምቦችን መጠበቅ እና በርቀት መስራት የሰው የአእምሮ ጤንነት ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡ እናንተ የራዲዮ ጋዘጠኞች የአእምሮ እና አካላዊ ጤንነታችሁን መከታተል እና ሥራችሁን በውጤታማነት መፈጸም እንድትችሉ ራሳችሁን መንከባከብ አለባችሁ፡፡ ይህን ለማድረግ የሚጠቅሟችሁ መንገዶች ከዚህ በታች አሉ፡-

 • መደበኛ እረፍት ይኑራችሁ፤ አቅም እንዳያንሳችሁ ድካምም እንዳይበዛባችሁ እራሳችሁን ተከታተሉ፡፡ ከሥራ ቀን በኋላ ዘና በማለት እንዳይታክታችሁ አድርጉ፡፡
 • የሥራ ኃላፊዎች የሠራተኞቻቸውን ሁኔታ መከታተል እና አስፈላጊውን ድጋፍ ማቅረብ አለባቸው፡፡ ለሠራተኞቹ የሚቀርበው ድጋፍ ስልክ መደወል፣ ማበረታታት፣ ተግዳሮቶቻቸውን ማዳመጥ እና ጥሩ ሥራቸውን ማመስገን ሊሆን ይችላል፡፡ የራዲዮ ጋዜጠኞች የተሠጣቸው ሥራ ላይ ደህንነት ካልተሰማቸው ለሥራ ኃላፊዎቻቸው መንገር አለባቸው፡፡
 • ኮቪድ-19 ላይ ዘገባ ስታዘጋጁ ባጠገባችሁ መደበኛ ሕይወታችሁን የሚያስታውሷችሁ የምታውቋቸው እና ደስ የሚሏችሁ ነገሮች ለምሳሌ የቤተሰብ ወይም ጓደኞች ፎቶ አጠገባችሁ በማስቀመጥ የአእምሮ ጤንነታችሁን አጎልብቱ፡፡
 • ስፖርት ሥሩ፣ ጤናማ ምግብ ተመገቡ፣ በቂ እንቅልፍ አግኙ፣ ብዙ ውሃ ጠጡ፡፡
 • በቻላችሁ መጠን መደበኛ የሥራ ፕሮግራም ይኑራችሁ፡፡

7. ስብሰባዎችን በርቀት አካሂዱ

በቡድን የምትሠሩ ከሆነ ፕሮግራማችሁ አየር ላይ ከመዋሉ በፊት የዝግጅት እና ሌሎች ስብሰባዎችን ማድረጋችሁ አይቀርም፡፡ ያለክፍያ ስብሰባ ማድረግ የምትችሉበት የኢንተርኔት ፕሮግራም ፈልጉ (ዋትስአፕ፣ ዙም፣ ስካይፕ፣ ጉግል ሃንግአውትስ፣ ወዘተ)፡፡ በነዚህ መንገዶች ስትሰበሰቡ ዳታ አጠቃቀማችሁን እና ወጭ ለመቆጠብ የድምጽ ተግባሩን ብቻ ተጠቀሙ፡፡ የስብሰባችሁን አጀንዳ ግልጽ አድርጉ እና አጀንዳውን አስቀድማችሁ በኢሜይል ለሁሉም ሰው እንዲደርስ አድርጉ፡፡ ከታች ያለውን ምሳሌ ተመልከቱ፡-

የዝግጅት ስብሰባ አጀንዳ
ርዕሰ ጉዳይ ዝርዝር
ሁሉን ሰው የሚመለከቱ ጉዳዮች ወደ ስብሰባው መግባት፣ በርቀት መሥራት ያለውን ተግዳሮት እና ስኬት መወያየት
ካለፈው ፕሮግራም ግብረ መልስ ምን ጥሩ ነበር፣ መሻሻል ያለበት ምንድን ነው፣ ሴቶች እና ወንዶች ለነሱ ጠቃሚ የሆኑ ጥራት ያላቸው መረጃዎችን ማግኘት እንዲችሉ ምን ተደርጓል
Dየዲፓርትመንት የአፈጻጸም ሪፖርት የያንዳንዱ ዲፓርትመንት (ዝግጅት፣ ቴክኒክ፣ አቅራቢ፣ ሥራ አመራር፣ ወዘተ) ተወካይ ለቀጣዩ ፕሮግራም ምን እንዳከናወኑ ሪፖርት እንዲያቀርቡ መጠየቅ
የጊዜ ሰሌዳ እና ማጠናቀቂያ ሰኣት መመደብ መረጃ ለመሰብሰብ፣ ቃለ መጠይቅ ለማድረግ፣ የድምጽ አርትኦት ለመሥራት፣ የዝግጅት ሥራዎች ቅደም ተከተል ለማዘጋጀት ለተለያዩ ሠራተኞች ሃላፊነት ስጡና ግልጽ ማጠናቀቂያ ሰኣት መድቡ
ሌላ ጉዳይ ች ጥያቄዎችን፣ አስተያየቶችን ወይምአሳሳቢ ጉዳዮችን በማስተናገድ ስብሰባውን አጠናቁ፡፡

ዝግጅቱ ያለእንከን እንዲጠናቀቅና አጠቃላይ የጣቢያው የሥራ እንቅስቃሴ በሚገባ እንዲከናወን በየምን ያህል ጊዜ የኢንተርኔት ስብሰባችሁን ማድረግ እንዳለባሁ በቡድን ወስኑ፡፡ የቡድን አባሎቻችሁ ያለባቸውን የግል እና የቤተሰብ ሃላፊነቶች ግንዛቤ ውስጥ አስገቡ፤ ለምሳሌ ሕጻናት ልጆች መንከባከብ እና የታመሙ የቤተሰብ አባላት መንከባከብ ያለባቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

ማስታወሻ፡- የዝግጅት ሥራዎች ቅደም ተከተል ቅጂ ለሁሉም የቡድኑ አባላት በቅድሚያ መላክ ያስፈልጋል፤ ይህ ቅደም ተከተል የፕሮግራም አቅራቢው፣ አዘጋጁ፣ ቴክኒሻኑ እና ፕሮግራሙ ላይ የሚሳተፉ ሁሉ በጊዜ ሰሌዳው አማካኝነት ሥራቸውን ለማቀናጀት ያስችላቸዋል፡፡ ሁሉንም የፕሮግራሙን ክፍሎችም ለማደራጀት እና በሰኣታቸው ጀምረው እንዲያልቁ ላመድረግ ያስችላል፡፡ በዚህ ርዕስ ዙርያ ተጨማሪ ለማንበብ የሚከተለውን የፋርም ራዲዮ ፕሮግራም አንብቡ፡- BH2 on developing a run sheet.

8. ምንጮችን ለማግኘት እና የተቀረጹ ድምጾችን አብሮ ለመጠቀም ተባበሩ

በመደበኛ የሥራ ሂደት ብዙ የራዲዮ ጋዜጠኞች ለራሳቸው ቀርጸው ያዘጋጁትን የድምጽ መረጃ ለሌሎች ጋዜጠኞች የመስጠት ፍላጎት ብዙም የላቸውም ምክንያቱም ጣቢያዎች ማንም ያልዘገበው የራሳቸውን ሥራ ማሰራጨት ይፈልጋሉ፡፡ አንድ የራዲዮ ጋዜጠኛ እራሱ ወይም የሥራ ባልደረቦቹ ያልቀረጹትን ቃለ መጠይቅ ወይም የድምጽ መረጃ ለአድማጮቹ ሳያሳውቅ መጠቀም የስነ ምግባር ጥሰት እና አሳሳች ነው፡፡ የጋዜጠኛ ሚና ምስክር መሆን ነው ስለዚህ የራሳቸው ይዘት ለማግኘትና ትክክለኛ ዘገባ ለማቅረብ በተቻለ መጠን መሞከር አለባቸው፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች በሚተገበሩባቸው ጊዜያት ግን አድማጮቻችሁ በማንኛውም መንገድ ቢሆን ሊያገኙት የሚገባቸው መረጃ ሊደርሳቸው ይገባል፡፡ ይህን ለማድረግ ከናንተ ጣቢያ ወይም ሌሎች ጣቢያዎች ውስጥ ካሉ ሌሎች ጋዜጠኞች ጋር በመተባበር የተለያዩ ግብዓቶችን ልትቀባበሉና ወይም በአካባቢያችሁ ስላሉ ሁኔታዎች አብራችሁ ፕሮግራም ልታዘጋጁ ትችላላችሁ፡፡ ለምሳሌ በአካባቢያችሁ የምርመራ ማእከል እያቋቋመ ወይም የፊት መሸፈኛ ጭንብል እያከፋፈለ ስላለ አንድ የጤና ባለስልጣን ወይም ከዚህ ባለስልጣን የተገኘን መረጃ ልትካፈሉ ትችላችሁ፡፡ ምናልባት ባካባቢችሁ ያለ ሙዚቀኛ ኮቪድ-19ን ስለመከላከል የዘፈነውን ዘፈን ልታጋሩ ትችላላችሁ፡፡ ይህ አሁን እያነበባችሁት ያለውን የፋርም ራዲዮ ትምህርትም ጠቃሚ ሆኖ ካገኛችሁት ልታጋሩ ትችላላችሁ፡፡ የመረጃውን ምንጭ እስከጠቀሳችሁ ድረስ ማካፈል ጠቃሚም ተገቢም ነው፡፡

በአካባቢያችሁ፣ በክልላችሁ ወይም በአገራችሁ ካሉ ሌሎች የራዲዮ ጋዜጠኞች ጋር መገናኘት የምትችሉባቸው ቡድኖች ካሉ በነዚህ ቡድኖች አማካኝነት መመካከር ትችላላችሁ፡፡ በሃገራችሁ ያለው የፋርም ራዲዮ የዋትስአፕ ቡድን እርስ በርስ ለመማማር እና ለመተጋገዝ በጣም የሚጠቅም መድረክ ነው፡፡ በሃገራችሁ ያለውን የፋርም ራዲዮ ተወካይ ጋር ተገናኙና የዋትስአፕ ቡድኑ ውስጥ እንዲመዘግባችሁ አድርጉ፤ ወይም ስማችሁን፣ አገራችሁን እና የራዲዮ ጣቢያችሁን ጠቅሳችሁ በሚከተለው ኢሜይል አድራሻ ጥያቂያችሁን ላኩ፡- radio@farmradio.org ፡፡

9. ከቤት ሆኖ ለመሥራት ጥሩ የኢንተርኔት ኮኔክሽን እንዲኖራችሁ አድርጉ

በዓለም ዙርያ ወሳኝ ያልሆኑ ንግድ ሥራዎች ከመዘጋታቸው ጋር ተያይዞ ለሞባይል ስልካችሁ ወይም ኮምፒዩተራችሁ የኢንተርኔት ዳታ ለመግዛት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ከተቻለ አስተማማኝ የሆነ የኢንተርኔት አገልገሎት ለማግኘት የሚያስፈልገውን ክፍያ ፈጽሙና ለቀናት ወይም ለሳምንታት ከቤት ሆናችሁ መሥራት የምትችሉበትን ሁኔታ ፍጠሩ፡፡ የሥራ ኃላፊዎቻችሁ ወጫችሁን እንደሚተኩላችሁ አስቀድሞ ማረጋገጫ ሳታገኙ ምንም ወጭ አታውጡ፡፡ ከርቀት ሆናችሁ በምትሠሩበት ወቅት የኢንተርኔት ወጫችሁን ጣቢያችሁ የማይሸፍን ከሆነ የሥራ ኃላፊዎች አካላዊ እርቀትን በጠበቀ መልኩ ሪፐርተሮች ወደ ጣቢያ የሚገቡበትን የጊዜ ሰሌዳ ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ ከላይ በተራ ቁጥር 6 እና 7 የተጻፈውን አንብቡ፡፡

አንድ የጋና ጋዜጠኛ ለአለቆቹ ማስገባት የሚችለውን የስልክ ሒሳብ የበጀት ጥያቄ ከታች ተመልከቱ፡፡

ዓይነት ዝርዝር ወጭ
የስልክ የድምጽ ሒሳብ 100 ደቂቃ የቀን ጥሪ እና ገደብ የለሽ የማታ እና የዊኬንድ ጥሪ የሜቲኤን (MTN) ጥቅል 10 የጋና ሴዲስ (ገንዘብ)
የስልክ የኢንተርኔት ጥቅል የሜቲኤን የዳታ ጥቅል 4GB ለ30 ቀናት 40 የጋና ሴዲ
ጠቃላይ ወጭ፡- 50 የጋና ሴዲስ

10. ፕሮግራሞቻችሁን ለማዘጋጀት የፋርም ራዲዮ ኢንተርናሽናል መረጃዎችን ተጠቀሙ

ፋርም ራዲዮ ኢንተርናሽናል ለራዲዮ የሚሆኑ እጅግ ብዙ ማቴሪያሎች ኢንተርኔት ላይ አሉት፡፡ ከነዚህም መካከል በየሳምነቱ ከፍተኛ ጥራት ያለው የራዲዮ ፕሮግራም ለማዘጋጀት የሚረዷችሁ ቃለ መጠይቆች፤ የድራማ ስክሪፕቶች፤ የግብር ጾታዊ እና ሌሎች ጉዳዮች ጠቅላላ መረጃዎች፣ ለጋዜጠኞች የሚሆኑ መመርያዎች፤ የአርሶ አደር ታሪኮች፤ እና ሌሎችም ብዙ ማቴሪያሎችን ታገኛላችሁ፡፡ እነዚህን ማቴሪያሎች በሚከተለው ሊንክ ገብታችሁ ማየት ትችላላችሁ፡- https://farmradio.fm/

በርቀት ስለመሥራት ተጨማሪ ትምህርት የት ማግኘት እችላለሁ?

Children’s Radio Foundation. COVID-19: Remote Reporting & Broadcast Tool Kit. April 2020. https://childrensradiofoundation.org/covid-19-remote-reporting-broadcast-toolkit/

Committee to Project Journalists. CPJ Safety Advisory: Covering the coronavirus outbreak. 6 April 2020. https://cpj.org/2020/02/cpj-safety-advisory-covering-the-coronavirus-outbr.php

Earth Journalism Network. Webinar: Staying safe while reporting on COVID-19. 15 April 2020. https://www.youtube.com/watch?v=KEcBYPGh8b0&feature=youtu.be

Wangui, Irene. Resources for African Journalists covering the pandemic. International Journalists Network. 9 April 2020. https://ijnet.org/en/story/resources-african-journalists-covering-pandemic

ምሥጋና
የጽሑፉ አዘጋጅ፡- ማክሲን ቤተሪጅ-ሞስ፣ ፍሪላንስ ጋዜጠኛ እና ከዚህ በፊት በፋርማ ራዲዮ ጋና የብሮድካስተር ሪሶርስስ አማካሪ
ይህ ጽሑፍ ከካናዳ መንግስት በግሎባል አፌይርስ ካናዳ በኩል በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ተዘጋጀ፡፡