የራዲዮ ጋዜጠኞች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ራሳቸውን እንዴት መጠበቅ እንደሚችሉ
ኮቪድ-19 ምንድን ነው?
ኮቪድ-19 በአዲሱ ኮሮናቫይረስ አማካኝነት የሚነሳ ተላላፊ በሽታ ነው፡፡ በታህሳስ 2012 በቻይና ውሃን ግዛት ውስጥ ተቀስቅሶ በፍጥነት በዓለም ዙርያ መሰራጨት ችሏል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት በመጋቢት 2012 ኮቪድ-19 አለም አቀፍ ወረርሽኝ መሆኑን አወጀ፡፡
በሽታው እንዴት ይሠራጫል?
ኮቪድ-19 ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች ወደ ሌሎች ሰዎች ይተላለፋል፡፡ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ሲያስላቸው፣ ሲያስነጥሱ ወይም ሲተነፍሱ በሚፈጠሩ የአፍና የአፍንጫ ፈሳሽ ፍንጣቂዎች አማካኝነት በሽታው ይሰራጫል፡፡ እነዚህ ፍንጣቂዎች በትንፋሽ አማካኝነት ወደ ሰውነት ውስጥ ይገባሉ ወይም በአካባቢ ላይ ያሉ እቃዎች እና የተለያዩ አካላት ላይ ያርፋሉ፡፡ ሰዎች እነዚህን ፍንጣቂዎች ወደ ሰውነታቸው በትንፋሽ አማካኝነት ሲያስገቡ ወይም ፍንጣቂዎቹ ያረፉባቸውን አካላት በእጃቸው ነክተው ከዚያ አይኖቻቸውን፣ አፍንጫቸውን ወይም አፋቸውን ሲነኩ በቫይረሱ ይበከላሉ፡፡
የበሽታው ምልክቶች ምንድን ናቸው?
የኮቪድ-19 ዋነኛ ምልክቶች ትኩሳት፣ ድካም እና ደረቅ ሳል ናቸው፡፡ ብዙዉን ጊዜ ምልክቶቹ ቀላል ሲሆኑ ቀስ በቀስ መታየት ይጀምራሉ፡፡ አንዳንድ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ምንም ምልክት አያሳዩም፣ ሕመምም አይሰማቸውም፡፡ አብዛኛዎቹ (80% ያህል) ምንም የተለየ ሕክምና ሳይደረግላቸው ይሻላቸዋል፡፡ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ከስድስቱ አንዱ በጣም ይታመማሉ፡፡ ሸምገል ያሉ ሰዎችና የልብ፣ የስኳር እና የደም ግፊት በሽታ ያለባቸው ሰዎች በጣም የመታመም እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ትኩሳት፣ ሳልና የመተንፈስ ችግር ያለባቸው ሰወች ሓኪም ማማከር ያስፈልጋቸዋል፡፡
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት እራሴን ለመጠበቅ ምን ማወቅ ያስፈልገኛል?
(ከታች በዝርዝር የተጻፈውን በማንበብ ስለነዚህና ሌሎችም ነጥቦች ተጨማሪ ግንዛቤ አግኙ)
- በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የራዲዮ ጋዜጠኞችን ለበሽታው የሚያጋልጧቸው ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
- የራዲዮ ጋዜጠኞች በኮቪድ-19 ዙርያ ያለ የተሳሳተ መረጃ ስርጭትን እንዴት መዋጋት ይችላሉ?
- የራዲዮ ጋዜጠኞች ራሳቸውንና ሌሎችን ሰዎች በቫይረሱ እንዳይያዙ እንዴት መከላከል ይችላሉ?
- የራዲዮ ጋዜጠኞች ስለ ወረርሽኙና ሌሎችም ጉዳዮች ዘገባ በሚያዘጋጁ ጊዜ ራሳቸውን ከጉዳት እንዴት መጠበቅ ይችላሉ?
- የራዲዮ ጋዜጠኞች ቢያማቸው ምን ማድረግ አለባቸው?
- የራዲዮ ጋዜጠኞች በወረርሽኙ ወቅት የአይምሮ ጤንነታቸውን እንዴት መጠበቅ ይችላሉ?
1. በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የራዲዮ ጋዜጠኞችን ለበሽታው የሚያጋልጧቸው ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
አንዳንድ የራዲዮ ጋዜጠኞች በተለያዩ ሁኔታዎች ከብዙ ሰዎች ጋር ቀጥታ ስርጭት ፕሮግራሞችን ስለሚያዘጋጁ ለኮቪድ-19 በሽታ የመያዝ እድላቸው ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ የራዲዮ ጋዜጠኞች እንደ መንግስት ቢሮዎች፣ ሆስፒታሎች፣ ክሊኒኮች እና የትራንስፖርት መናኸርያዎች የመሳሰሉ ዋነኛ በሽታ አስተላላፊ የሆኑ ቦታዎች ላይ በመገኘት ዘገባ ማዘጋጀት ስለሚጠበቅባቸው በቫይረሱ የመበከል ዕድላቸው ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ጋዜጠኞች እራሳቸውን ለመከላከል መውሰድ የሚችሏቸው አንዳንድ እርምጃዎች አሉ፡፡ (#3ን ይመልከቱ)
2. የራዲዮ ጋዜጠኞች በኮቪድ-19 ዙርያ ያለ የተሳሳተ መረጃ ስርጭትን እንዴት መዋጋት ይችላሉ?
ስለኮቪድ-19 የተሳሳቱ መረጃዎች ከቫይረሱ ፈጥነው ሊሰራጩ ይችላሉ፡፡ ጋዜጠኞች የቫይረሱን ስርጭት፣ የበሽታውን ምልክቶች፣ ሕክምና እና ሌሎችም ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ የተሳሳቱ መረጃዎችን በመዋጋት የራሳቸውን ሚና መጫዎት ይችላሉ፡፡
በመጀመርያ ጋዜጠኞቹ ስለኮቪድ-19 ያላቸውን መረጃ ሙሉ በሙሉ ማረጋገጥ እና እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ወይም የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ባለስልጣናት ካሉ የታወቁና የታመኑ ምንጮች የተገኘ መሆኑን ማረገጋጥ አለባቸው፡፡ በመቀጠል ጋዜጠኞቹ በማሕበረሰቦቻቸው ውስጥ የተሰራጩ ሃሰተኛ መረጃዎችን የጤና ባለሙያዎችን ጋብዘው ውሸቱን እንዲያመክኑ እና ትክክለኛ መረጃ እንዲሰጡ በማድረግ መዋጋት አለባቸው፡፡ ሦስተኛ ጋዜጠኞች አድማጮቻቸውን የሚሰሙትን መረጃ መርምረው እንዲጣሩ እና ትክክል መሆኑን የማያውቁቱን መረጃ እንዳያሰራጩ ማበረታታት አለባቸው፡፡ ለተጨማሪ መረጃ የፋርም ራዲዮን BH2 on fake news አንብቡ፡፡
ስለኮቪድ-19 የሚሠራጩ አሳሳች መረጃ ምሳሌዎች እና መረጃው ለምን ውሸት ወይም አሳሳች እንደሆነ ከነማብራርያው ከዚህ በታች ተመልከቱ:-
1. ፀረ-ተህዋሲን (አንቲባዮቲክስ) መድሃኒቶች ኮቪድ-19ን ለመከላከልም ለማከምም አይችሉም፡፡ ፀረ-ተህዋሲያን ለባክቴሪያ እንጂ ለቫይረስ ሕክምና አያገለግሉም፡፡ ኮቪድ-19 ቫይረስ ስለሆነ ለመከላከልም ሆነ ለህክምና አንቲባዮቲክስ መጠቀም አይገባም፡፡ ነገር ግን ለኮቪድ-19 ሕክምና ሆስፒታል ከገቡ ሌሎች በሽተዎችን ለመከላከል ፀረ-ተህዋሲያን ሊሰጥ ይችላል፡፡
2. ክሎሮኩዊን ኮቪድ-19ን አያድንም፡፡ ክሎሮኩዊን የወባ መድሃት ቢሆንም ለኮቪድ-19 ሕክምና ያገለግል እንደሆነ ለማረጋገጥ ሙከራ እየተደረገበት ነው፡፡ ነገር ግን ፈውስ አይሰጥም፣ ሙከራውም ቀጥሏል፡፡ አስተውሉ፡- ክሎሮኩዊን ብዙዉን ጊዜ ምንም ጉዳት የማያስከትል መድሃኒት ቢሆንም አንዳንድ አሉታዊ ተጓዳኝ ተጽእኖ (ሳይድ ኢፌክት) ማምጣቱ ግን ተዘግቧል፡፡
3. ለ10 ሰከንድ እና ከዚያ በላይ ምንም ሳያስሉ ትንፋሽን መያዝ ከኮቪድ-19 ነጻ መሆንን አያሳይም፡፡ ኮቪድ-19 የያዛቸው የመሰላቸው ሰዎች ቤታቸው እንዲቀመጡና በአካባቢቸው ያሉ የጤና ባለስልጣናትን በማሳወቅ የሕክምና ክትትል እንዲያገኙ የዓለም ጤና ድርጅት ይመክራል፡፡ ኮቪድ-19 እንዳለባችሁ እና እንደሌለባችሁ ለማረጋገጥ ዋነኛው መንገድ የላቦራቶሪ ምርመራ ነው፡፡ ትንፋሽን ለመቆጣጠር በመሞከር ማረጋገጥ አይቻልም፣ እንዲያውም አደገኛ ሊሆን ይችላል፡፡
4. ኮቪድ-19ን ሊከላከሉ ወይም ሊያድኑ ይችላሉ እየተባለ በሐሰት የሚነገርላቸው ነገሮች አሉ፡፡ ከነዚህም መካከል ሎሚ እና እርሾ ቀላቅሎ መጠጣት፤ የብርቱካን ወይም የሎሚ ልጣጭ ቀቅሎ እንፋሎቱን ማሽተት፣ አትክልትና ፍራፍሬ የመሳሰሉ “አልካላይን” ምግቦችን መመገብ፣ በጨው ወይም አቼቶ መጉመጥመጥ፣ እና የእጽዋት ሕክምና መከታተል የመሳሰሉ ይገኙበታ፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ግን በኮቪድ-19 ላለመያዝ እና የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚከተሉትን እርምጃዎች መውሰድ ያስፈልጋል፡- እጅን በሳሙና ወይም አልኮል ባለው ሳኒታይዘር ቶሎ ቶሎ መታጠብ፣ ከሚያስላቸው እና ከሚያስነጥሳቸው ሰዎች ቢያንስ የአንድ ሜትር እርቀት መጠበቅ፣ ፊትን አለመንካት እና ሲያስላችሁ እና ሲያስነጥሳችህ አፍና አፍንጫችሁን በክርናችሁ ወይም በሶፍት መሸፈን ናቸው፡፡
ሊንኩን በመጫን ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ይቻላል፡- key information on COVID-19 for broadcasters.
3. የራዲዮ ጋዜጠኞች ራሳቸውንና ሌሎችን ሰዎች በቫይረሱ እንዳይያዙ እንዴት መከላከል ይችላሉ?
ሰዎች እራሳቸውንና ሌሎችን ለመከላከል ማድረግ የሚችሏቸው መሰረታዊ የጤና መመርያዎች አሉ፡፡ እነሱም፡-
• እጃችሁን ቶሎ ቶሎ መታጠብ፡፡ እጆቻችሁን በሳሙናና ውሃ ወይም አልኮል ባለው ሳኒታይዘር ቶሎ ቶሎ አጽዱ፡፡ ለምን? እጆቻችሁን በሳሙናና ውሃ ወይም አልኮል ባለው ሳኒታይዘር መታጠብ እጆቻችሁ ላይ ያሉ ቫይረሶችን ይገድላል፡፡
• አካላዊ እርቀትን መጠበቅ፡፡ ከቤታችሁ ውጭ የሆኑ ሰዎችን በአካል ላለመገናኘት ሞክሩ፡፡ በጣም አስፈላጊ ከሆነ ግን እንደ አገራችሁ መንግስት መመርያ ከአንድ እስከ አራት ሜትር እርቀት ለመጠበቅ ሞክሩ፡፡ ለምን? አንድ ሰው ሲያስለው ወይም ሲያስነጥሰው ቫይረሱ ሊኖርባቸው የሚችሉ የአፍና አፍንጫ ፈሳሽ ፍንጣቂዎች ይረጫሉ፡፡ በጣም ቅርበት ካላችሁ እነዚህን ፍንጣቂዎች ወደ ውስጥ ልትተነፍሷቸው ትችላላችሁ፡፡
Image source: https://www.cnn.com/2020/03/24/health/six-feet-social-distance-explainer-coronavirus-wellness/index.html
• አይኖቻችሁን፣ አፍንጫችሁን እና አፋችሁን አትንኩ፡፡ ለምን? እጆች ብዙ ነገሮችን ስለሚነኩ ቫይረሱን ሊይዙ ይችላሉ፡፡ አንዴ ከተበከሉ በኋላ ቫይረሱን ወደ አይኖች፣ አፍንጫ አና አይኖች ሊያስተላልፉ ይችላሉ፡፡ ከዚያ ወደ ሰውነት ሊገባ እና በሽታ ሊያመጣ ይችላል፡፡
• ጥሩ የአተነፋፈስ ስነምግባር ተከተሉ፡፡ ሲያስነጥሳችሁ ወይም ሲያስላችሁ አፍና አፍንጫችሁን በክንዳችሁ ወይም በሶፍት ሸፍኑ፡፡ የተጠቀማችሁበትን ሶፍት ወዲያው አስወግዱ፡፡ ለምን? ፍንጣቂዎች ቫይረሱን ያሰራጫሉ፡፡ ጥሩ የአተነፋፈስ ስነምግባር ስትከተሉ በዙርያችሁ ያሉ ሰዎችን ከኮቪድ-19 እና ጉንፋን እና ፍሉ ከሚያመጡ ቫይረሶች ትከላከላላችሁ፡፡
• ሰው ከሚበዛባቸው ቦታዎች እራቁ፤ እነሱም ገበያ እና ሌሎች የህዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች እና የሕዝብ ትራንስፖርት የመሳሰሉ ናቸው፡፡ ለምን? አንዳንድ ሰዎች የሚታይ ምልክት ሳይኖርባቸው ቫይረሱ ሊኖርባቸው ስለሚችሉ ከሌሎች ሰዎች በቅርብ እርቀት መገኘት በበሽተው የመያዝ እድልን ከፍ ያደርጋል፤ ስለዚህ የጤና ባለስልጣናት ችግር አለመኖሩን እስኪያሳውቁ ድረስ ከሌሎች ሰዎች ጋር መገናኘትን ማስወገድ የተሻለ ነው፡፡ ወደ ውጭ መውጣት ካስፈለጋችሁ የፊት መሸፈኛ ጭንብል በመልበስ እራሳችሁን እና ሌሎችን ጠብቁ፡፡ ቫይረሱ በማስነጠስ እና በመሳል ስለሚተላለፍ ጭንብል መልበስ እራሳችሁን እና ሌሎችን ለመጠበቅ ይረዳል – ስለጭንብል አጠቃቀም ከስር ያለውን የመጨረሻውን ነጥብ ተመልከቱ፡፡
• ስልኮቻችሁን እና ሌሎች እቃዎችን አጽዱ፡፡ ማንኛውንም እቃ ወይም ምግብ፣ በተለይ ደግሞ ማይክሮፎን፣ መቅረጸ-ድምጽ፣ እስክርቢቶ፣ እርሳስ፣ ስልክ፣ የኪስ ቦርሳ ወይም ማንኛውንም ደጋግማችሁ የምትነካኩትን እቃ ከነካችሁ በኋላ እጆቻችሁን ከጀርም አጽዱ፡፡
• ሰላምታ ስትለዋወጡ ጥንቃቄ አድርጉ፡፡ ኮቪድ-19 እንዳይይዛችሁ ሰላም ስትባባሉ አካላዊ ንክኪን አስቀሩ – አትተቃቀፉ፣ አትጨባበጡ፡፡ ጥንቃቄ የተሞላው ሰላምታ ማለት እጅን ማወዛወዝ፣ ጭንቅላትን መነቅነቅ፣ ክርን ማጋጨት ወይም እጅ መንሳት ነው፡፡
• ጭንብል ልበሱ፡፡ ጭንብል መልበስ በቀላሉ ለመተንፈስ ከማስቻሉም በላይ ስታወሩ፣ ስታስነጥሱ እና ሲያስላችሁ የምራቅ ፍንጣቂዎች እንዳይበተኑ ይከላከላል፡፡ ጭንብሉን በትክክል መልበሳችሁን ለማረጋገጥ የአፍንጫችሁ ዘንግ ላይ እና አገጫችሁ ስር በትክክል ይግጠም፡፡ ጭንብሉን አትንኩት፤ ስታዎልቁትም ማንገቻዎቹን ይዛችሁ እንጂ ከፊት ለፊት ይዛችሁ አትሳቡ፡፡ ጭንብሉን ካወለቃችሁ በኋላ እጃችሁን በሳሙናና በሙቅ ውሃ ታጠቡ ወይም አልኮል (ከ60% በላይ ኢታኖል ወይም 70% አይሶፕሮፓኖል) ያለው ሳኒታይዘር ተጠቀሙ፡፡ ጭንብሉ ሲረጥብ ወዲያውኑ በአዲስ፣ ንጹህና ደረቅ ጭንብል ቀይሩት፡፡ ማስታዎሻ፡- ጭንብል መጠቀም ሌሎቹን መከላከያ መንገዶች ስለማያስቀር ከላይ ከተዘረዘሩት እርምጃዎች ጋር አብሮ መፈጸም አለበት፡፡
ማስታዎሻ፡- አንዳንድ ሰዎች ምንም ምልክት ሳያሳዩ ኮቪድ-19 ሊኖርባቸው ይችላል፡፡ ይሄ ማለት እራሳቸውም ሳያውቁ በሽታውን ለሌሎች ሰዎች ሊያስተላልፉ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም እነዚህ የተዘረዘሩት የጤንነት እና የደህንነት ጥንቃቄዎች እራስንም ሆነ ሌሎችን ሰዎች ለመጠበቅ አስፈላጊ ናቸው፡፡
4. የራዲዮ ጋዜጠኞች ስለ ወረርሽኙና ሌሎችም ጉዳዮች ዘገባ በሚያዘጋጁ ጊዜ ራሳቸውን ከጉዳት እንዴት መጠበቅ ይችላሉ?
የራዲዮ ጋዜጠኞች ሥራቸውን ሳያቆሙ እራሳቸውን መከላከል የሚችሉባቸው ብዙ መንገዶች አሉ፡፡
• ከቻላችሁ ከቤታችሁ ሥሩ፡፡ ከቤት ሆናችሁ የድምጽ አርትኦት ሥራ፣ በስልክ ወይም በዋትስአፕ ቃለ መጠይቅ ማድረግ እና የቤት ኮምፒዩተራችሁን እና ሞባይል ስልካችሁን በመጠቀም መረጃ ልትፈልጉ/ሪሰርች ልታደርጉ ትችላላችሁ፡፡
• የሥራ ቦታችሁን እና መሣርያዎቻችሁን ሁል ጊዜ ከጀርም የጸዱ አድርጉ፡፡ ወደ ራዲዮ ጣቢያ መሄድ ካለባችሁ መሣርያዎቻችሁን እና የሥራ ቦታችሁን ከ60% በላይ ኢታኖል ወይም 70% አይሶፕሮፓኖል ባለው ሳኒታይዘር አጽዱ፡፡ በቤትና በቢሮ የምትሠሩበትን አካባቢም ሁል ጊዜ አጽዱ፡፡ እናንተ የምትነኳቸውን ቦታዎች ሁሉ ሌላ ሰው ወይም እቃ ከነካቸው ወዲያው ማጽዳት አለባችሁ፡፡ ከተቻለ በእጅ የሚነካ ሳይሆን ጠረጴዛ ላይ የሚቀመጥ ማይክሮፎን ተጠቀሙ፡፡ ማይክሮፎኑን በትክክል ለማጽዳት (ከታች ያለውን ስዕል ተመልከቱ) ወንፊቱን ንቀሉት፣ ከዚያ ስፖንጁን አውጡ (ስፖንጁ እንደሽፋን ከማገልገል ባለፈ የጎላ ጥቅም የለውም) ከዚያ በሌላ ቀይሩት ወይም በሳኒታይዘር አጽዱት፡፡ የማይክሮፎኑን አካል (መያዣውን) ወይም መቀመጫውን እና አብረው ያሉ ማንኛውንም ቁልፎች እና ማብሪያና ማጥፊያዎች ሁሉ ከጀርም የጸዱ አድርጉ፡፡
• የተለያዩ ማይክሮፎኖች ተጠቀሙ፡፡ በአካል ላለመገናኘት ሞክሩ፣ በጣም አስፈላጊ ከሆነ ግን ለራሳችሁና ቃለ መጠይቅ ለምታደርጉለት ሰው የተለያዩ ማይክሮፎኖቸን ተጠቀሙ፡፡ ከመጠቀማችሁና ከተጠቀማችሁ በኋላ በሳኒታይዘር እና በሚተጠብ ጨርቅ አጽዷቸው፡፡
• አሳሳች መረጃን ተዋጉ፡፡ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ አሳሳች መረጃዎችን ለመዋጋት የተሻለው መሣርያ ትክክለኛ ዘገባ ማድረግ ነው፡፡ ጋዜጠኞች ስለቫይረሱ ሲያወሩ መረጃዎቻቸው ትክክለኛ መሆናቸውን በጥልቀት መመርመር፣ ያለ አድልኦ መዘገብ እና አላስፈላጊ የሆኑ የዘር፣ የዜግነት እና የብሄር ማንነት ጥቆማዎችን በማስወገድ የተዛባ አመለካከት እንዳይፈጠር ማድረግ አለባቸው፡፡ የሐሰት መረጃዎችን ለመለየት እና ለመዋጋት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ሊንኩን ይጫኑ፡- BH2 on fake news.
• በአካል ተገናኝታችሁ ቃለ መጠይቅ ማድረግ ካለባችሁ ረጅም ሰልፊ-ስቲክ ወይም ዘንግ በመጠቀም አካላዊ እርቀትን ጠብቁ፡፡ አካላዊ እርቀትን መጠበቅ ካልተቻለ ቃለ መጠይቁን ሰርዙ፡፡ አካላዊ አርቀትን ከመጠበቅ በተጨማሪ ፊት ለፊት ሳይሆን ወደ ጎን ቁሙ፡፡ በተቻለ መጠን በገጽ የሚደረጉ ቃለ መጠይቆችን ከቤት ውጭ አድርጉ፡፡ ቤት ውስጥ ማድረግ ካለባችሁ የአየር ፍሰት ያለበት ቦታ ላይ ለምሳሌ ክፍት መስኮት አካባቢ ሆናችሁ ተነጋገሩ፡፡
• ለቫይረሱ ከተጋለጡ አካባቢዎች ለመራቅ አስቡ፡፡ ጋዜጠኞች ዋናውን ዘገባ የሚያኙት ከጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች ቢሆንም የራሳችሁን ጤንነት እና ደህንነት ለመጠበቅ ስትሉ ላለመሄድ ብታስቡ ይሻላል፡፡ ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ ሊሎች ጉዳዮችን ሽፋን መስጠት ይሻላል፡፡ ይሄ ማለት ወደ ጤና ጣቢያዎች፣ ምርመራ ቦታዎች፣ የአስከሬን ማቆያ ቦታዎች፣ ለይቶ ማቆያ ጣቢያዎች፣ በሕዝብ የተጨናነቁ (የከተማ) አካባቢዎች እና የታመሙ ሰዎች ወዳሉባቸው ቤቶች አለመሄድ ማለት ነው፡፡ በርግጥ ይሄንን ውሳኔ መወሰን ያለባችሁ ከራዲዮ ጣቢያው ሥራ ሃላፊዎች ጋር በመመካከር ነው፡፡
• ከአረጋውያን እና የጤና ችግር ካለባቸው ሰዎች ጋር የሚኖር ግንኙነት፡፡ እነዚህ ሰዎች ለኮቪድ-19 ያላቸው ተጋላጭነት ከፍተኛ ስለሆነ በስልክ ወይም በዋትስአፕ ቃለ መጠይቅ ብታደርጉላቸው ተመራጭ ይሆናል፡፡ እናንተ ራሳችሁ እንደዚህ አይነት ሰው ከሆናችሁ ከቤታችሁ ባትወጡ ይሻላል፡፡
• ከሥራ ባልደረቦቻችሁ እና ከቤተሰብ አባሎቻችሁ ጋር አቅዱ፡፡ ሥራ ላይ እያላችሁ ብትታመሙ እንዴት ድጋፍ ሊደረግላችሁ እንደሚችል ለመወሰን የሥራ አመራር ቡድኑን ዕቅድ ተነጋገሩበት፤ይህንን ስታደርጉ ረዘም ላለ ጊዜ ራሳችሁን ልትለዩ ወይም ለይቶ ማቆያ ውስጥ ልትገቡ እንደምትችሉ አስታውሱ፡፡
ኮቪድ-19ን በጥንቃቄ እንዴት መሸፈን እንደሚቻል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሚቀጥለውን ሊንክ ይጫኑ፡- working remotely for radio broadcasters.
5. የራዲዮ ጋዜጠኞች ቢያማቸው ምን ማድረግ አለባቸው?
ቤታችሁ በመቆየት ራሳችሁን ከቤተሰብ አባሎቻችሁና ከሌሎች ሰዎች ለዩ፡፡ አስፈላጊ ከሆነ ብቻ (እንደ መተንፈስ ችግር፣ ትኩሳት እና የማይለቅ ደረቅ ሳል የመሳሰሉ የበሽታው ምልክቶች እየባሱ ከሄዱ) የሕክምና እርዳታ ጠይቁ፡፡
6. የራዲዮ ጋዜጠኞች በወረርሽኙ ወቅት የአይምሮ ጤንነታቸውን እንዴት መጠበቅ ይችላሉ?
የራዲዮ ጋዜጠኞች የቫይረሱን ስርጭት፣ በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎችን እና ለሰዎችና ማህበረሰቦች ደህንነት ሲባል የሚደረጉ ክልከላቸዎችን ስለሚዘግቡ የራዲዮ ጋዜጠኞች ሥራ በኮቪድ-19 ወቅት በተለየ መልኩ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሥራችሁን በአጥጋቢ ሁኔታ መሥራት እንድትቀጥሉ ስለ አይምሮ እና አካላዊ ጤንነታችሁ ማሰብ እና አስፈላጊውን እንክብካቤ ለራሳችህ ማድረግ ይገባችኋል፡፡ ከዚህ በታች ያሉት ስትራቴጂዎች ይህን ለማድረግ ይረዷችኋል፡-
- ቶሎ ቶሎ እረፍት አድርጉ፤ አቅማችሁ እንዳይቀንስ እና ድካም እንዳይሰማችሁ ተከታተሉ፡፡ ከሥራ ሰዓት በኋላ ለመዝናናት እና ረጋ ለማለት ሞክሩ፡፡
- የሥራ ሃላፊዎች የሥራ ባልደረቦቻቸውን በቅርብ እየተከታተሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይገባል፡፡ የራዲዮ ጋዜጠኞች ስለሚመደቡበት ሥራ ስጋት ከተሰማቸው ለአለቆቻቸው መንገር አለባቸው፡፡
- ለኮቪድ-19 ሽፋን ስትሰጡ በአጠገባችሁ መደበኛ ሕይወትን የሚያስታውሱ እቃዎችን ወይም የቤተሰብ እና የጓደኞቻችሁን ፎቶዎች በማስቀመጥ የአይምሮ ጤንነታችሁ እንዲጎለብት እና ውጥረታችሁ እንዲቀንስ አድርጉ፡፡
- ስፖርት ሥሩ፣ ጤናማ ምግቦችን ተመገቡ፣ በቂ እንቅልፍ አግኙ፣ ብዙ ውሃ ጠጡ፡፡
- በተቻለ መጠን መደበኛ የእለት ከእለት የሥራ እንቅስቃሴ ይኑራችሁ፡፡
በኮቪድ-19 ወቅት ስለራዲዮ ጋዜጠኛ ጤንነት እና ደህንነት ተቸማ መረጃ የት ማግኘት እችላለሁ?
Committee to Protect Journalists, 2020. CPJ Safety Advisory: Covering the coronavirus outbreak. https://cpj.org/2020/02/cpj-safety-advisory-covering-the-coronavirus-outbr.php
Harrison, Sylvie, and Cuddeford, Vijay, 2017. BH2: How to plan and produce effective emergency response programming for farmers. Farm Radio International. http://scripts.farmradio.fm/radio-resource-packs/105-farm-radio-resource-pack/plan-produce-effective-emergency-response-programming-farmers/
Lewis, Katya Podkovyroff, 2020. Mental and physical health of reporters during COVID-19. https://ijnet.org/en/story/mental-and-physical-health-reporters-during-covid-19
ምሥጋና
የጽሑፉ አዘጋጅ፡- ማክሲን ቤተሪጅ-ሞስ፣ ፍሪላንስ ጋዜጠኛ እና ከዚህ በፊት በፋርማ ራዲዮ ጋና የብሮድካስተር ሪሶርስስ አማካሪ
ይህ ጽሑፍ ከካናዳ መንግስት በግሎባል አፌይርስ ካናዳ በኩል በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ተዘጋጀ፡፡